ቀጥታ፡

የኃይል መቆራረጥን ለመፍታት የኤሌክትሪክ ማከፋፈያ መሰረተ ልማቶችን ሊያዘምን ይገባል - የከፍተኛ ኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ደንበኞች

አዲስ አበባ  /ኢዜአ/ የካቲት 27/2015 የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሚያጋጥመውን የኃይል መቆራረጥ ለመፍታት የኤሌክትሪክ ማከፋፈያ መሰረተ ልማቶችን ሊያዘምን እንደሚገባ የከፍተኛ ኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ደንበኞች አመለከቱ። 

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ተግባራዊ እያደረገ ባለው የሦስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ አስመልክቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ በአዲስ አበባ ውይይት አካሄዷል።

የወንጂ ስኳር ፋብሪካ የፋብሪካ ዘርፍ ሥራ አስኪያጅ ልዑልሰገድ ተሾመ እንደገለጹት፤ "የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች በአብዛኛው እድሜ ጠገብ ናቸው።ይህም ፋብሪካዎች የሚያስፈልጋቸውን የኃይል አቅርቦት ያለምንም መቆራረጥ እንዳያገኙ አድርጓል" ብለዋል።

የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች በተደጋጋሚ የሚጠገኑበት ጊዜ መስፋቱ በፋብሪካው ምርት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ ነው ብለዋል።


 

በመሆኑም ተቋሙ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶችን በተገቢው በመለየትና የማስተካከል ስራ ማከናወን እንደሚገባው ተናግረዋል።

የካፒታል ሲሚንቶ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አብዱራህማን አብዱልባቂ በበኩላቸው፤ በከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ደንበኞች የሚገጥመው የኃይል መቆራረጥና የመሰረተ ልማት ብልሽት በኢኮኖሚያዊ እድገት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር ገልጸዋል።

ለኃይል መቆራረጥና ለመሰረተ ልማት ብልሽት አፋጣኝ መፍትሔ መስጠት እንደሚያስፈልግ እና   በዘርፉ ላይ ያሉ ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሽፈራው ተሊላ፤ በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱንና ይህንንም ፍላጎት ለማርካት ተቋሙ ከ2015 በጀት ዓመት ጀምሮ ለሶስት ዓመት የሚቆይ  ስትራቴጂ ዕቅድ ቀርጾ ወደ ተግባር መገባቱን ጠቁመዋል።

ይህንንም ተከትሎ የከፍተኛ ኤሌክትሪክ ኃይል ደንበኞች ከኃይል አቅርቦት መቆራረጥ ጋር ተያይዞ የሚያጋጥመውን ችግር ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የኤሌክትሪክ ማከፋፈያ መሰረተ-ልማቶችን የማዘመን ሥራ በመከናወን ላይ መሆኑንም ተናግረዋል። 

ደንበኞች ከተቋሙ ማግኘት የሚፈልጉትን  አገልግሎቶች በተገቢው መልኩ እንዲያገኙ በቴክኖሎጂ የተደገፉ አሰራሮችን ለመተግበር አገልግሎቱ ጥረቶችን እያደረገ ነው ብለዋል፡

የኢትዮጵያ ኤሌትሪክ  ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ብዙወርቅ ደምሴ በበኩላቸው፤ ለከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚዎች የኃይል አቅርቦትን ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ይሁንና አብዛኞቹ የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማቶች መልሶ ግንባታን የሚጠይቁ መሆናቸውና የንዑስ ጣቢያዎች(Sub Stations) ተደራሽ አለመሆን ችግሩን እንዳባባሰው አመልክተዋል።

አምራች ኢንዱስትሪዎች ተቀራራቢ ባልሆኑ አካባቢዎች መኖራቸውም የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችሉ መሰረተ-ልማቶችን ለማሟላት አዳጋች አድርጎታል" ብለዋል።

ይህንንም ችግር ለማቃለል ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በመሆን የኤሌክትሪክ ማከፋፈያ መሰረተ-ልማቶችን የማዘመን ብሎም መልሶ የመገንባት ስራ በመከናወን ላይ እንደሚገኝም ነው አቶ ብዙወርቅ ያስረዱት።

ለኃይል መቆራረጥ ምክንያት ከሆኑ ጉዳዮች መካከል አንዱ የመሰረተ-ልማት ስርቆት መሆኑን የተናገሩት ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚው ዜጎች በየአካባቢያቸው የሚገኙትን የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማቶችን እንዲጠብቁ ጥሪያቸውን አቅርበዋል። 

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት  በአሁኑ ሰዓት ካሉት  4 ነጥብ 5 ሚሊየን ደንበኞች ውስጥ 36 ሺህ የሚጠጉት የከፍተኛ ኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ደንበኞች መሆናቸውን ከተቋሙ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም