በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በመምከር የጋራ መግባባት ላይ መድረስ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በመምከር የጋራ መግባባት ላይ መድረስ ይገባል
አዲስ አበባ /ኢዜአ/ የካቲት 27/2015 በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በመምከር የጋራ መግባባት ላይ ማተኮር እንደሚገባ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ታዬ ደንደአ ገለጹ።
በኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ የሰላም ግንባታ እና አብሮነት ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ ዛሬ ተካሄዷል።
የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ታዬ ደንደአ፤ ሰላምን መጠበቅና መንከባከብ "የጥቂት ተቋማት ወይም ቡድኖች" ድርሻ ብቻ ሳይሆን የሁሉንም ዜጎች ትብብርና አብሮነት የሚጠይቅ ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ የሚስተዋሉ ችግሮችን ሕብረ ብሔራዊነትና ብዝሃነትን በሚያስተናገድ መልኩ በዘላቂነት መፍታት ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።
በመሆኑም ልዩነቶችን ለመፍታት በአንድነት ጥላ ስር በመሰባሰብ በምክክር የጋራ መግባባት በመፍጠር አንድነትን ማጠናከር ይገባል ብለዋል።
በኢትዮጵያ የኔዘርላንድ አምባሳደር ሄንክ ጃን ቤከር፤ እውነተኛ እና ሁሉን አቀፍ ውይይት ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው ኢትዮጵያ የያዘቻቸው እቅዶችም ከተሳኩ ውጤት ያመጣሉ ብለዋል።
በመሆኑም የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ሂደት የተሳካ እንዲሆን የሁሉንም ጥረትና ትብብር እንደሚጠይቅ ገልጸዋል።
የተሳካ ውጤት ለማምጣት መሰል የውይይቶች መድረኮች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውና በዚህ ረገድ የኔዘርላንድ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አመልክተዋል።