ቀጥታ፡

መንግስት የኦዲት ግኝት በሚታይባቸው ተቋማት ላይ የማስተካከያ እርምጃ በመውሰድ ተጠያቂነትን ማስፈን አለበት - የፌደራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት

 አዲስ አበባ የካቲት /ኢዜአ/ 27/2015  መንግስት የኦዲት ግኝት በታየባቸው ተቋማት ላይ  የማስተካከያ እርምጃ በመውሰድ ተጠያቂነትን ማስፈን እንደሚገባው የፌደራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ገለጸ፡፡

የመስሪያ ቤቱ ምክትል ዋና ኦዲተር አቶ አበራ ታደሰ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ተቋማት መንግስት የሚያወጣቸውን ህጎች ደንቦችና መመሪያዎችን አክብረው  ሊሰሩ ይገባል፡፡

ከዚህ ውጭ የሚሰሩ የመንግስት ተቋማት ደግሞ የኦዲት ግኝት እየታየባቸው እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የውስጥ አሰራር ስርዓት አለመዘርጋት፣ የባለሙያዎች አቅም ውስንነት፣ የኦዲት ግብረ መልስ ተቀብሎ አለማስተካከል ለኦዲት ግኝት መንስኤዎች ናቸው ብለዋል።

የፌደራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት "በዓለም አቀፍ የኦዲተር መስሪያ ቤት ደረጃ እና በህገ መንግስቱ መሰረት "ከወገንተኝነት  ነጻ በሆነ አግባብ" የኦዲት ስራውን እያከናወነ ነው" ሲሉም ገልጸዋል። 

"የተቋሙ ባለሙያዎችም ነጻ"ና ገለልተኛ በመሆን ኃላፊነትና ተጠያቂነት መኖሩን አክብረው ስራቸውን ያከናውናሉ ነው ያሉት አቶ አበራ።

የኦዲተሮች በሚያቀርቡት የኦዲት ሪፖርት ላይ አስተያየት ከመስጠት ውጭ ሪፖርቱን እንዲያስተካክሉ ወይም እንዲቀይሩ የሚያስገድዳቸው አካል እንደሌለ ተናግረዋል።


 

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ቋሚ ኮሚቴ "በዓለም አቀፍ የኦዲት አሰራር መሰረት ስራውን ነፃ እና ገለልተኛ" ሆኖ መስራት እንዲችል በተፎካካሪ ፓርቲ አባል እንዲመራ መደረጉን ጠቅሰው፤ ይህም "የኦዲት ስራን በአግባቡ ለማከናወን ሚና የጎላ ነው" ብለዋል።

የፌደራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት የኦዲት ሪፖርቶች በሚመለከታቸው አካላት ቁጥጥር ተደርጎባቸው የማስተካከያ እርምጃ ሊወሰድባቸው እንደሚገባ አመልክተዋል።

በመሆኑም መንግስት የሚቀርቡለትን የፋይናንስ፣ የክዋኔ እና ሌሎችም የኦዲት ግኝት ሪፖርቶች መሰረት የማስተካከያ እርምጃ በመውሰድ ተጠያቂነትን ማስፈን እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

ኦዲት ተደራጊ ተቋማትም በቀረበባቸው የኦዲት ሪፖርት ላይ የሚሰጣቸውን ግብረ መልስ የድርጊት መርሐግብር በማውጣት የማስተካከያ ርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው ምክትል ዋና ኦዲተሩ አሳስበዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም