የዝናብ ውሃን የማጠራቀም ፕሮጀክትን በድርቅ ተጎጂ ለሆኑ አከባቢዎች ሁነኛ መፍትሄ ለማድረግ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የዝናብ ውሃን የማጠራቀም ፕሮጀክትን በድርቅ ተጎጂ ለሆኑ አከባቢዎች ሁነኛ መፍትሄ ለማድረግ እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 27/2015 የዝናብ ውሃን በማጠራቀም ፕሮጀክት ለድርቅ ተጋለጭ ለሆኑ አከባቢዎች ሁነኛ መፍትሄ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ሃብታሙ ኢተፋ ገለጹ።
"ግድቤን በደጄ" በሚል መርህ ሃሳብ በኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በሙከራ ደረጃ ፕሮጀክቱ ተሞክሮ ውጤታማ ሆ
ኗል።
ከዚህ ተሞክሮ በመነሳትም በድርቅ ተጎጂ በሆነው በቦረና ዞንና በአማራ ክልል ጎንደር ዞን አካባቢዎች የፕሮጀክት ግንባታ እየተካሄደ እንደሚገኝም የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ሐብታሙ ኢተፋ፤ "ግድቤን በደጄ" የዝናብ ውሃን የማጠራቀም ፕሮጀክት በቦረና ዞን በሚገኙ ትምህርት ቤቶችና መንደሮች በመተግበር ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
በፕሮጀክቱ የዝናብ ውሃን በማሰባሰብ በዘመናዊ መንገድ ወደ ተገነባ ገንዳ በማጠራቀም ንጽህናው በተጠበቀ መልኩ በአነስተኛ ማሽን በማውጣት ሕብረተሰቡ እንዲጠቀም ይደረጋል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ውስጥ በሁሉም አከባቢዎች የዝናብ ውሃ ካለፈ በኋላ የሚታየውን የውሃ ችግር ለመቅረፍ ግድቤን በደጄ የተባለው ፕሮጀክትን ለመተግበር ዕቅድ መነደፉንም ገልጸዋል።
በተለይም ፕሮጀክቱ ዝናብ አጠር ለሆኑና በድርቅ ተጎጂ ለሆኑ አካባቢዎች ላይ ያለውን ውሃ ችግር ለመፍታት ሁነኛ መፍትሄ እንደሚሆንም ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ በቦረና ዞን ስምንት ትምህርት ቤቶችና በአንድ አካባቢ ተግባራዊ በመደረግ ላይ መሆኑን ጠቁመው፤ የግንባታ ሂደቱም በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛልም ብለዋል፡፡
ግድቤን በደጄ ፕሮጀክት በአነስተኛ ጉልበት ንጹህ ውሃን በደጅ ለማግኘት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለውም ገልጸዋል።
በቀጣይ የውሃ እጥረት ባለባቸውና በተደጋጋሚ በድርቅ ተጎጂ ለሆኑ ሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች የፕሮጀክቱ ትግበራ በተጠናከረ መልኩ ይቀጥላል ሲሉም ተናግረዋል።
የቦረና ዞን ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት በድርቁ ምክንያት ከዚህ ቀደም ሲጠቀሙበት የነበረው የውሃ አማራጭ ሁሉ ደርቆ መቸገራቸውን ገልጸዋል።
ይህ በአከባቢያቸው በመገንባት ላይ የሚገኙ ፕሮጀክቶችም ሲጠናቀቁ የውሃ ችግራቸውን እንደሚቀርፍላቸው ተስፋ ማድረጋቸውንም ገልጸዋል፡፡
በተጠናቀቁ ግንባታዎች ላይም የዝናብ ውሃ እስኪያገኙ ድረስ በቦቴ ውሃ እንዲጨመርላቸውም ጠይቀዋል፡፡
በቦረና ዞን የተገነቡት የውሃ ገንዳዎች ከ120 ሺህ እስከ 200 ሺህ ሊትር ውሃ የመያዝ አቅም እንዳላቸው ገልጸው፤ አንድ ጊዜ በሚይዙት ውሃ ከስድስት ወር በላይ ተጠቃሚ ያደርጋሉ ተብሏል።