ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንና የፓኪስታን ባለሃብቶች ልዑካን ቡድን እየተወያዩ ነው

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 27/2015 የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን እና የፓኪስታን ባለሃብቶች የልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት አማራጮችና ምቹ ሁኔታዎች ላይ እየተወያዩ ነው።

በውይይቱ ላይ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ለሊሴ ነሜ፣ የሁለቱ ሀገራት አምባሳደሮች፣ የፓኪስታን የኢንቨስትመንት እና ንግድ ልዑካን ቡድን አባላት፣ የኢትዮጵያ የንግድ ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ተወካዮችንና የዘርፉ ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ናቸው።

በፓኪስታን የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ጀማል በከር በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ ሁለቱ ሀገራት መልካም የሆነ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አላቸው።

የልዑካን ቡድኑ በኢትዮጵያ ጉብኝት ማድረጉ በሀገራቱ መካከል ያለውን ግንኙነት ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግር መሆኑን ተናግረዋል።

ሀገራቱ በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ፣ በሠላም ማስከበር፣ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን መከላከል እና በሌሎች ጉዳዮች ላይ በጋራ እየሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል።


 

እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ የኢትዮጵያ መንግሥት ከፓኪስታን ጋር በትብብር መስራቱን እንደሚያጠናክርም አረጋግጠዋል።

በኢትዮጵያ የፓኪስታን አምባሳደር ሻዛብ አባስ በበኩላቸው፤ የሁለቱን ሀገራት የኢኮኖሚ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ የልዑካን ቡድኑ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት የዚሁ አካል መሆኑን አብራርተዋል።

በግብርና ዘርፍ፣ በኃይል አቅርቦት፣ በመስኖ ልማት፣ በማዕድንና በሌሎች ዘርፎችም በጋራ መስራታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል።

የፓኪስታን ንግድና ኢንቨስትመንት ልዑክ ሰባ አንድ አባላትን አካትቶ ትላንት ማምሻውን አዲስ አበባ መግባቱ ይታወቃል።

 


 


 


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም