ቱባ የባህል ስፖርቶችን በማልማትና በማስፋት የህዝቦችን አብሮነትና መተሳሰብ ለማጎልበት እየተሰራ ነው--አቶ ቀጀላ መርዳሳ - ኢዜአ አማርኛ
ቱባ የባህል ስፖርቶችን በማልማትና በማስፋት የህዝቦችን አብሮነትና መተሳሰብ ለማጎልበት እየተሰራ ነው--አቶ ቀጀላ መርዳሳ
ሚዛን አማን (ኢዜአ) የካቲት 26/ 2015 በኢትዮጵያ ያሉትን ቱባ የባህል ስፖርቶች በማልማትና በማስፋት የህዝቦችን አብሮነትና መተሳሰብ ለማጎልበት እየተሰራ መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ቀጀላ መርዳሳ ተናገሩ።
20ኛው ሀገር አቀፍ የባህል ስፖርቶች ውድድር እና 16ኛው የባህል ፌስቲቫል በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በሚዛን አማን ከተማ ዛሬ ተጀምሯል።
በማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ ንግግር ያደረጉት የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ቀጀላ መርዳሳ እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ የብዝሃ ብሔር መገኛ እንደመሆኗ በርካታ የባህል ስፖርቶች አሏት።
እነዚህን የባህል ስፖርቶች በማልማትና በማስፋት የህዝቦች የእርስ በእርስ ትስስርና አንድነት እንዲጎለብት ሚኒስቴሩ በትኩረት እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
የባህል ስፖርቶች ውድድር የመተሳሰብና የመፈቃቀር እሴትን በህዝቦች ልብ ውስጥ የሚያስቀምጥ መሆኑንም አመላክተዋል።
የባህል ስፖርት እንዲስፋፋ ሚኒስቴሩ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እንደሚወጣ የገለጹት አቶ ቀጀላ፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎችን ማስፋፋት አንዱ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ያለ ተግባር መሆኑን ጠቁመዋል።
የባህል ስፖርቶች የሚመሩባቸው ሕጎችና ደንቦችን በመሰነድ ተጠብቀው ለትውልድ እንዲሸጋገሩና በዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን እንዲጨምሩ የሚያስችሉ ተግባራት እየተሰሩ መሆኑንም ገልጸዋል።
እንደ አቶ ቀጀላ ገለጻ፣ ስፖርቱን ማጠናከር ከተቻለ በሀገራችን የተጀመረው ዘላቂ ሰላምና ጠንካራ አንድነት ግንባታን ዕውን ማድረግ ይቻላል።
በየአካባቢው ያለ የባህል ስፖርት እንዲጎለበት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ በበኩላቸው፣ "የባህል ስፖርት የህዝቦችን ወግና ባህል የሚያጎለብት የሰላምና የወንድማማችነት መገለጫ ነው" ብለዋል።
የባህል ስፖርቶች ውድድር የሀገራችንን ቱባ ባህሎች ከማስተዋወቅ ባለፈ ለሀገር ሰላምና አንድነት አስተዋጿቸው የጎላ መሆኑንም ገልጸዋል።
ውድድሩ በተለይ የመከባበርና የመተሳሰብ ባህልን ከማጎልበት አንጻር ትምህርት የሚወሰድበት መሆን እንዳለበትም ነው ያመለከቱት።
በመሆኑም ተወዳዳሪዎች በውድድር ሜዳ የሚያሳዩት የመከባበርና የመተሳሰብ እሴት በቀጣይ ወደየአካባቢያቸው ሲሄዱ በማጎልበት በኅብረተሰቡ ውስጥ አንድነትና ወንድማማችነትን እንዲያጠናክሩ አስገንዝበዋል።
ውድድሩ ተሳታፊዎች የክልሎቻቸውን አኩሪ ባህል በማስተዋወቅ ልምድ ለመለዋወጥ መልካም አጋጣሚ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የኢትዮጵያ የባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ሰለሞን አስፋው ናቸው።

ፕሬዚዳንቱ "ከአባቶቻችን የተረከብነውን አንጡራ የባህል ሀብት በማስተዋወቅ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ እንሰራለን" ሲሉም ገልጸዋል።
ትውልዱ ይህን ዕውን የማድረግ ሃላፊነት እንዳለበት ጠቁመው፣ ተወዳዳሪዎች በየባህሎቻቸው ያለውን የውድድር ሥነስርዓት ጠብቆ በመፎካከር ባህሎች ጎልተው እንዲወጡ የድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
በመክፈቻው ሥነ ስርዓቱ ላይ በተካሄደ የሴቶች የትግል ውድድር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጋር የተገናኘ ሲሆን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአሸናፊነት ተወጥቷል።
ዛሬ በይፋ የተጀመረው 20ኛው የባህል ስፖርቶች ውድድር በ11 ባህላዊ የስፖርት አይነቶች የሚካሄድ ሲሆን ውድድሩም እስከ መጋቢት 3 ቀን 2015 ድረስ በባህል ፌስቲቫል ታጅቦ እንደሚቆይ ታውቋል።