ቀጥታ፡

ዓለም አቀፉ የንግድ ተቋም ‘ካፒታል ኢኩዊሊብረም’ በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ እና ሌሎች የፋይናንስ መስኮች እንዲሰማራ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 25/2015 ዓለም አቀፉ የንግድ ተቋም ‘ካፒታል ኢኩዊሊብረም’ በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ እና ሌሎች የፋይናንስ መስኮች ላይ እንዲሰማራ በመንግስት ጥሪ ቀረበለት።

‘ካፒታል ኢኩዊሊብረም’ የኢነርጂ መሰረተ ልማትን ጨምሮ በዘላቂ የፋይናንስ ዘርፎች ላይ የሚሰራ የንግድ ተቋም ነው።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ እና የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋ መቀመጫውን ሀንጋሪ ካደረገው ተቋም ጥምር መስራች ዶክተር ፒተር ናጊ ጋር በኳታር ዶሃ ውይይት አድርገዋል።

ውይይቱ በዶሃ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መዘጋጀቱም ተገልጿል።


 

ምክክሩ ‘ካፒታል ኢኩዊሊብረም’ በኢትዮጵያ የኢነርጂ ዘርፍ ላይ በሽርክና በሚሰራበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ለተቋሙ ጥምር መስራች ዶክተር ፒተር ናጊ በኢትዮጵያ የኢንቨሰትመንት እድሎች በተለይም በታዳሽ ኃይል እና ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዘርፎች ያሉ አማራጮች በዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።


 

መንግስት በአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ በባንክ እና ፋይናንስ ዘርፍ ላይ የውጭ ባለሀብቶች  እንዲሳተፉ ለማድረግ እና ለካፒታል ገበያ ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል።

ውይይቱ ‘ካፒታል ኢኩዊሊብረም’ የተሰኘው ዓለም አቀፍ የንግድ ተቋም ከመንግስት ጋር በመንግስት እና በግል አጋርነት ማዕቀፍ መስራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ መሆኑን ከወጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።


 

በሌላ ዜና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ እና የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋ በኳታር ዶሃ እየተገነባ ያለውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን ጎብኝተዋል።

የቤተ ክርስቲያኗ ግንባታ በ 1 ሺህ 846 ሜትር ስኩዌር ላይ ያረፈ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን የግንባታው መሬት ከኳታር መንግስት የተሰጠ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም