የባህል ስፖርቶችን በማልማት አገራዊ አንድነትን ማጠናከር ይገባል--የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የባህል ስፖርቶችን በማልማት አገራዊ አንድነትን ማጠናከር ይገባል--የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር
ሚዛን አማን (ኢዜአ) የካቲት 25/2015 የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የባህል ስፖርቶችን በማልማት አገራዊ አንድነትን ማጠናከር እንደሚገባ ገለጸ።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሚዛን አማን ከተማ ነገ የሚጀመረው 20ኛው ሀገር አቀፍ የባህል ስፖርቶች ውድድርና 16ኛው የባህል ፌስቲቫል አካል የሆነው የባህል ስፖርቶች ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይት እየተካሄደ ነው።
በውይይቱ ላይ የተገኙት የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት የባህል ስፖርቶች ህዝቡ ከስር መሰረቱ ይዞት የመጣው ባህላዊ እሴቶች መገለጫዎች ናቸው።
የህዝብ ሀብት የሆኑ የባህል ስፖርቶችን በማልማት ለሰላምና ለአገራዊ አንድነት ማጠናከሪያነት መጠቀም አስፈላጊ በመሆኑ እየተሰራበት እንደሆነ አመላክተዋል።
ስፖርት ህዝቦችን ለተመሳሳይ ዓላማ በማገናኘት የእርስ በርስ ትስስር ለመፍጠር ያለው ፋይዳ የጎላ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ ሕብረ ብሔራዊት አገር በመሆኗ የባህል ስፖርቶች ውድድር ኢትዮጵያውያንን እርስ በርስ ከማስተዋወቅ ባሻገር የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ የሚያግዝ መድረክ መሆኑን ጠቁመዋል።
በአግባቡ ማልማትና ማስተዋወቅ ከተቻለ የባህል ስፖርቶች የቱሪዝም ሀብት የመሆን ከፍተኛ አቅም እንዳላቸውም አስገንዝበዋል።
20ኛው የባህል ስፖርቶች ውድድርና የባህል ፌስቲቫል ላይ ለመሳተፍ ከሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች የመጡ ልዑካን ልምድ መለዋወጥ እንዳለባቸው ነው የተናገሩት።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አህመዲን አወል በኩላቸው የባህል ስፖርት ካለበት ደረጃ ከፍ ብሎ ማደግ አለበት።
የባህል ስፖርት ያለውን ፋይዳ በመገንዘብ ዘርፉን ማሳደግ የሚያስችሉ አቅጣጫዎች ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሰራ ገልጸዋል።
የክልሉ መንግስት የዘንድሮ የባህል ስፖርቶች ውድድር ዓላማውን ጠብቆ በስኬት እንዲከናወን መዘጋጀቱንም ተናግረዋል።
የሚዛን አማን ከተማ ከንቲባ አቶ ግሩም ተማም በእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክታችው እንግዶች የአካባቢውን የተፈጥሮ ሀብት እያደነቁ፤ ባህሉን በማየት የራሳቸውን አጋርተው ያማረ ቆይታ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።