ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አቪየሽን ዩኒቨርሲቲ በቀጣዩ ዓመት በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር ሊጀምር ነው

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 25/2015 የቀድሞው የኢትዮጵያ አቪየሽን አካዳሚ የአሁኑ የኢትዮጵያ አቪየሽን ዩኒቨርሲቲ በቀጣዩ ዓመት በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር እንደሚጀምር አስታወቀ።  

የዩኒቨርሲቲው ተጠባባቂ ፕሬዝዳንቱ ካሴ ይማም ለኢዜአ እንደገለጹት፣ የአቪየሽን አካዳሚው ላለፉት 65 ዓመታት ለአየር መንገዱ ስኬታማነት ጉልህ ድርሻ ሲወጣ ቆይቷል።


 

አካዳሚው የፓይለት፣ የበረራ መስተንግዶ፣ የቴክኒሻንና የአገልግሎት ሠራተኞችን ጨምሮ ከ15 ሺህ በላይ የአቪዬሽን ሙያተኞችን ማሰልጠኑን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ትልቁና ሥመ-ጥር የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ማደግና የዘርፉን እድገት ተከትሎ አካዳሚው ወደ ዩኒቨርስቲ ማሳደግ አስፈልጓል ብለዋል።

ይህንንም ተከትሎ አካዳሚው አሁን ላይ የዘርፉን ቴክኖሎጂዎችና ሌሎች አስፈላጊ ግብዓቶችን በማሟላት ወደ ዩኒቨርስቲ ማደጉን ነው ተጠባባቂ ዳይሬክተሩ የተናገሩት።


 

በዚህም የአቪየሽን ዩንቨርሲቲው በአምስት አይነት የትምህርት መርኃ ግብሮች ሥልጠናዎችን መስጠት የሚያስችለውን እውቅና ማግኘቱን አብራርተዋል።

የትምህርት መርኃ ግብሮቹ በኤርክራፍት ሜንቴናንስ፣ ኢንጂነሪንግ፣ በኤሮማቴክ ኢንጂነሪንግ፣ በአቪየሽን ማኔጅመንት፣ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፎች ትኩረት ያደርጋል ብለዋል።

በሁለተኛ ዲግሪ በአቪየሽን ማኔጅመንት ሥልጠና ለመሥጠት መዘጋጀቱንም ጠቁመዋል።


 

በቅርቡ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማሰልጠን ምዝገባ እንደሚካሄድ ገልጸው ዩኒቨርስቲው በ2016 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ይገባል ነው ያሉት።

ይህንንም ተከትሎ ከኢትዮጵያ፣ አፍሪካ፣ ከእስያና ከሌሎች የዓለም ክፍሎች ለሚመጡ የዘርፉ ባለሙያዎች ሥልጠና እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።


 

ዩኒቨርስቲው እስካሁን በተቋሙ ሲሰጡ የቆዩትን ሥልጠናዎች እንደሚያስቀጥልም አክለዋል።

የአቪየሽን ዩንቨርሲቲው አየር መንገዱን ከማጠናከር ባለፈ በጋራ የሚሰራባቸውን አየር መንገዶች ለማጠናከር አስተዋጽዖው ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የ'ፓን አፍሪካኒዚም እሳቤን' እውን ለማድረግ የሚያደርገውን ጥረት ወደ ፊት በማስኬድ በኩል አስተዋጽኦው የላቀ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ አካል የሆነው የኢትዮጵያ አቪየሽን ዩኒቨርሲቲ በቅርቡ ሁለተኛውን የአቪየሽን ማሰልጠኛ በአዋሳ መገንባቱ ይታወሳል።


 

በቀጣይም በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ በአፋር፣ በአሶሳና በሌሎች ክልሎች በተመሳሳይ የአቪየሽን ማሰልጠኛዎችን ለመክፈት ዝግጅት እየተካሄደ መሆኑን ተጠባባቂ ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም