የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በፈረንሳይኛና ትግሪኛ ቋንቋዎች መረጃዎችን ተደራሽ የሚያድረግ ድረ-ገጽ አስጀመረ

986

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 25/2015፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ መረጃዎችን በፈረንሳይኛና ትግሪኛ ቋንቋዎች ተደራሽ የሚያደርግ አዲስ ድረ-ገጽ አስጀመረ።

አዲሱን ድረ-ገጽ በይፋ ስራ ያስጀመሩት የተቋሙ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤና በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ ትዕግስት ሀሚድ ናቸው።


የተቋሙ ዌብ አድሚኒስትሬተር ሄኖክ አብይ በማስጀመሪያ ስነ-ስርዓቱ ላይ እንደገለጹት አዲሱ ድረ-ገጽ መረጃዎችን በተለያዩ ቋንቋዎች በእኩል ጥራት ለማድረስ የሚያስችል ሆኖ የተገነባ ነው።


 


የተቋሙን ብራንድ መሰረት ባደረገ መልኩ የተዘጋጀው ድረ-ገጹ ከመረጃ ጥራትና ደኅንነት አንጻርም አስተማማኝ ሆኖ አገልግሎት እንዲሰጥ በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር አማካኝነት መገንባቱንም ገልጸዋል።


ድረ-ገጹ ከዚህ ቀደሞ በተቋሙ ሲሰራባቸው የነበሩትን እንግሊዝኛ ፣ አረብኛ ፣ አማርኛ እና አፋን ኦሮሞን ጨምሮ በአዲስ መልኩ በቅርቡ የተጀመሩትን ፈረንሳይኛና ትግሪኛ ቋንቋዎችን በማካተት አገልግሎት እንዲሰጥ ሆኖ መደራጀቱን አስታውቀዋል።


የኢዜአ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ እንዳሉት ኢዜአ የኢትዮጵያን ገጽታ የሚገነቡ ሀገራዊ ጉዳዮችን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ተደራሽ የሚያደርጉ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል ።


አሁን ይፋ የሆነው አዲስ የድረ-ገጽ ይሀንኑ አላማ ለማስፈጸም የሚያግዝ ነው ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው አስተማማኝነቱና ደህንነቱ የተጠበቀ ሆኖ ዘመናዊ አገልግሎት ማቅረብ እንዲያስችል በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር መገንባቱን ተናግረዋል።


በቀጣይም ኢዜአ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ጋር በዘርፉ ልማት ዙሪያ የሚያከናውናቸውን ስራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል። 


የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ ትዕግስት ሀሚድ በበኩላቸው ተቋማቸው የመገናኛ ብዙሃን ተቋማትን ደህንነት ለማስጠበቅ የሚያስችሉ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።


ከኢዜአ ጋርም በዘርፉ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን ለመከላከል በጋራ ከመስራት ባለፈ በቀጣይም በዚህና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ግንኙነት የሚያሳድጉ ተግባራትን እንደሚያጠናክሩ ገልጸዋል።


በድረ-ገጹ የስራ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ የሁለቱም ተቋማት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች ተገኝተዋል።


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም