የኢትዮጵያ ንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን የምርት ብልሽትን የሚከላከል ማቀዝቀዣ መጋዘን ያካተተ ሁለገብ ሕንጻ ሊያስገነባ ነው

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 25/2015 የኢትዮጵያ ንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን የአትክልት እና ፍራፍሬ ምርት ጥራቱና ደህንነቱ የተጠበቀ ማድረግ የሚያስችል  ማቀዝቀዣ መጋዘን የያዘ ሁለገብ ሕንጻ ሊያስገነባ መሆኑን አስታውቋል።

የሁለገብ ሕንጻ ግንባታው የመሰረት ድንጋይ ማስቀመጥ ስነ-ስርዓት ዛሬ በአቃቂ ቃሊቲ  ክፍለ ከተማ ተካሄዷል።


 

የሕንጻው ግንባታ በሁለት ምዕራፍ ተከፍሎ በአራት ዓመታት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ የገለጹት የኢትዮጵያ ንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አቻ ደምሴ ናቸው።

የሁለገብ ህንጻው ግንባታ በ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ወጪ እንደሚከናወንም ጨምረው ገልጸዋል።


 

ሕንጻው ባለ አስር ወለል ሲሆን ማቀዝቀዣ፣ የገበያ ማዕከል፣ ላቦራቶሪዎች፣ እና የመኪና ማቆሚያ ስፍራን ያካተተ እንደሆነ ተነግሯል።

የሁለገብ ሕንጻው መገንባት የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት ያለ ብልሽት ጥራቱ እና ደህንነቱ ተጠብቆ ለገበያ የማቅረብ እድልን እንደሚያሰፋ  የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አቻ ደምሴ ገልጸዋል።


 

የህንጻው መገንባት በአትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍ ላይ ያለውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ፋይዳው ወሳኝ መሆኑንም አክለዋል።

በፈራፍሬና አትክልት ገበያ ላይ ከትራንስፖርት ጀምሮ ያለውን የማቀዝቀዣ ስርዓት ለማስተካከል በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም