ባለፉት ስድስት ወራት በሀገራዊ ዕድገትና ገጽታ ግንባታ ላይ ጠንካራ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ስራ ተሰርቷል--የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

1577

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 25 ቀን 2015   በኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ወራት በአገራዊ ዕድገትና ገጽታ ግንባታ ላይ ጠንካራ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ስራ መከናወኑን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ።

በመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት የተዘጋጀው የፌዴራልና ክልል ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ተቋማት የበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ የስድስት ወራት የዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው።


 

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ኢትዮጵያ በጫናዎች ውስጥ ሆናም በተለያዩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ተጨባጭ ለውጥ ተመዝግቧል።

ኢትዮጵያ በስንዴ ልማት፣ በመልካም አስተዳደር ሥራዎች፣ በአገልግሎት አሰጣጥና በዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች አበረታች ውጤት ተገኝቷል ብለዋል።

ሰላምና መረጋጋትን በማስፈን በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እንደ አገር የተመዘገቡ ስኬቶች መሆናቸውን የገለጹት ሚኒስትሩ ለእነዚህ ስኬቶች የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን አስተዋፅኦ ድርሻ የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።

በመንግስት እና ሕወሓት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት መሰረት እንዲዝ እንዲሁም በሌሎች አገራዊ ስኬቶች ላይ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ ጠንካራ ስራ አከናውኗል ነው ያሉት።

"በኢትዮጵያ አክራሪነትና ጽንፈኝነት ውስብስብ ችግሮችን በመፍጠር ተጽእኖ አሳድረዋል" ሲሉ የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ይሄንን በመመከትም አበረታች ስራ መሰራቱን አመልክተዋል።

"የዜጎች ሰላም ወጥቶ በሰላም መመለስ እረፍት የሚነሳቸው የውስጥና የውጭ ታሪካዊ ጠላቶች ኢትዮጵያን ለማመስ የሚያደርጉትን እኩይ ሙከራ ማክሸፍ ይገባል"  ብለዋል።

"ኢትዮጵያ የሚያጋጥሟትን ፈተናዎች በድል ተወጥታ የጀመረችውን የብልጽግና ጉዞ እውን እንድታደርግ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ በተናበበ አኳኋን መምራት የሚጠበቅብን ወቅት ላይ ደርሰናል" ሲሉ ገልጸዋል። 

ኢትዮጵያ በዲሞክራሲያዊ ሽግግር ላይ መሆኗን የገለጹት ዶክተር ለገሰ፤ ሂደቱን የተሳለጠ ለማድረግ በዘርፉ የሚከናወኑት ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ብለዋል።

በቀጣይም አክራሪነትና ፅንፈኝነትን በቅንጅት በመመከት የኢትዮጵያን ሕዝብ የሚመጥን የሚዲያ እና ኮምኒኬሽን ስራ መስራት እንደሚገባም ሚኒስትሩ አሳስበዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም