ቀጥታ፡

የጤና ሥርዓቱ ስኬቶችን እንደ ወረት እየወሰደና ጉድለቶችን እያረመ በተደመረ አቅም እየዘመነ ነው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 20/2019(ኢዜአ)፦ የጤና ሥርዓቱ ስኬቶችን እንደ ወረት እየወሰደና ጉድለቶችን እያረመ በተደመረ አቅም በየጊዜው እየዘመነ መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ፍሬህይወት አበበ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ባዮሜዲካል መሐንዲሶችና ቴክኒሻኖች ማህበር የ2019 ጠቅላላ ዓመታዊ ጉባዔውን አካሂዷል።

በዚህ ወቅት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ፍሬህይወት አበበ እንዳሉት፤ የጤና አገልግሎት ጥራትና ፍትሐዊነት ተደራሽነትን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት በትኩረት እየተከናወኑ ነው።
 

ከ30 ዓመት በላይ ያገለገለው የኢትዮጵያ የጤና ፖሊሲ ተከልሶ መከላከልና አክሞ ማዳን ላይ እንዲያተኩር መደረጉንና ይህንም ተከትሎ የተለያዩ አዋጆች መፅደቃቸውን አንስተዋል።

የጤና ሥርዓቱ በየጊዜው እየዘመነ፣ ያሳካናቸውን ውጤቶች እንደ ወረት እየወሰደ፣ ጉድለቶችን እያረመ የሚሄድ ሥርዓት ነውም ብለዋል።

የጤና አገልግሎት ሥርዓቱ ሁልጊዜ እየተደመረ የሚሄድ ውጤት የሚያመጣ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የባዮሜዲካል መሐንዲሶችና ቴክኖሎጂስቶች የጤናው ዘርፍ የጀርባ አጥንት መሆናቸውን ገልጸዋል።

በሀገራችን ከ50 ሺህ በላይ የግልና የመንግስት ጤና ተቋማት እንደሚገኙ ጠቅሰው፤ በእነዚህ ተቋማት ያሉ የህክምና መሣሪያዎች በአግባቡ እንዲሰሩና እንዲጠገኑ የባለሙያዎቹ ሚና ወሳኝ ነው ብለዋል።

በባለፈው ዓመት በጤና ተቋማት በምልልስ ከ220 ሚሊዮን በላይ ተጠቃሚዎች መመዝገባቸውን ጠቅሰው፤ ማኅበሩ ከሚኒስቴሩ ጋር በመሆን በዘመቻ ከ26 ሺህ በላይ የሕክምና መሣሪያዎችን በመጠገን ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ማዳን መቻሉን ተናግረዋል።

ከኮቪድ በኋላ በዘመቻ ተገዝተው ወደ ክልሎች የተላኩ መሣሪያዎችንም በእነዚህ ባለሙያዎች እንዲተከሉ በማድረግ ወደስራ መግባታቸውን ጠቅሰዋል።

ሚኒስቴሩ ከማኅበሩ ጋር በመሆን የኢትዮጵያ የሕክምና መሣሪያዎች ስያሜ ሥርዓትንና የሕክምና መሣሪያዎች አስተዳደር ስትራቴጂን ለመጀመሪያ ጊዜ ማዘጋጀቱን ጠቅሰዋል። 

የኤካ ኮተቤ አጠቃላይ ሆስፒታል ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶክተር መገርሳ አለሙ በበኩላቸው፤ የባዮሜዲካል መሐንዲሶችና ቴክኖሎጂስቶች ለህክምና አገልግሎቶች መሠረት መሆናቸውን ገልጸዋል።

ለጤና ምርመራ የሚያስፈልጉ የህክምና መሳሪያዎች የሚፈትሹትና የሚጠግኑት በእነርሱ በመሆኑ ለአገልግሎት ጥራትና ደኅንነቱ የላቀ አስተዋፅኦ የሚያበረክቱ ናቸው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ባዮሜዲካል መሐንዲሶችና ቴክኒሻኖች ማህበር ፕሬዝዳንት ኢንጂነር አሸብር ወርቁ እንደገለጹት፤ የማኅበሩ ዋና ዓላማ የባለሙያዎች ድምጽ መሆንና አቅማቸውን ማጎልበት ነው። 

የባዮሜዲካል መሐንዲሶች ትምህርት በጅማና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲዎች ብቻ ይሰጥ እንደነበር አንስተው፤ አሁን ላይ በአምስት ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርቱ እየተሰጠ መሆኑን ጠቅሰዋል። 

አሁን ላይ ከአምስት ሺህ በላይ ባዮሜዲካል መሐንዲሶችና ቴክኒሻኖች እንዳሉ አንስተው፤ ማኅበሩ በየዓመቱ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት እስከ 400 መሣሪያዎችን በመጠገን ከ120 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደሚያድን ገልጸዋል።

የማህበሩ ምክትል ፕሬዝዳንትና የግላንዶ ባዮሜዲካል ሶሉሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ይዲዲያ ስለሺ፣ ባለሙያዎቹ መሣሪያዎችን ከመለየት እስከ መትከል፣ መጠገንና ካሊብሬት ማድረግ ድረስ ጉልህ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል።

ተቋማቸው መሣሪያዎችን ሀገር ውስጥ በመገጣጠምና በማምረት የጤና ዘርፍ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እንደሚሰራም አስረድተዋል።

የማህበሩ ሥራ አስፈጻሚ አባልና የደብሊውኤምጂ ባዮሜዲካል ኢንጂነሪንግ ኃላፊ አቶ ምኒልክ አጋ፤ የሕክምና መሣሪያዎችን በሀገር ውስጥ ማምረት ለሀገር ሉዓላዊነት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል። 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም