በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የምርጥ ዘር አቅርቦትን በራስ አቅም ለመሸፈን እየተደረገ ያለው ጥረት ውጤታማ ሆኗል - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የምርጥ ዘር አቅርቦትን በራስ አቅም ለመሸፈን እየተደረገ ያለው ጥረት ውጤታማ ሆኗል
ጂንካ፤ ህዳር 19/2019(ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የምርጥ ዘር አቅርቦትን በራስ አቅም ለመሸፈን እየተደረገ ያለው ጥረት ውጤታማ መሆኑ ተገለፀ።
በምርጥ ዘር ብዜት ስራው የተሰማሩ አርሶ አደሮች እና የግል ባለሀብቶችም የምርጥ ዘር አቅርቦቱና ቴክኖሎጂውን የማስፋፋት ስራው ውጤታማ መሆኑን ለኢዜአ ገልጸዋል ።
በክልሉ አሪ ዞን የኩሬ ቀበሌ አርሶ አደር ፀጋዬ ታደሰ፥ በክልሉ የምርጥ ዘር አቅርቦት ድርጅት ድጋፍ የበቆሎ ምርጥ ዘር ብዜት ስራ ላይ መሳተፋቸውን ጠቁመው ከቴክኖሎጂ የማስፋፋት ስራው በቂ ልምድና ዕውቀት ማግኝታቸውን ገልጸዋል ።
ለምርጥ ዘር ብዜት የሚቀርብላቸው የበቆሎ ዝርያ ከአከባቢው ዝርያዎች ሲነፃፀር በአጭር ጊዜ ምርት የሚሰጥ፣ የአየር ንብረት ለውጡን የሚቋቋም እና በአነስተኛ የዝናብ መጠን በእጥፍ ምርት ለማግኝት የሚያስችል ነው ብለዋል።
በክልሉ የምርጥ ዘር ብዜት ስራ ላይ የተሰማራው የናባስ እርሻ ልማት ድርጅት ተወካይ መቆያ መብራቴ፤ በመንግሥት በሚደረግላቸው የክህሎትና የምርጥ ዘር ድጋፍ በ14 ሄክታር ላይ በሙከራ ደረጃ በቆሎና የቦለቄ ምርጥ ዘር ማባዛታቸውን ገልጸዋል ።
ለምርጥ ዘር ብዜት የተመረጡ የበቆሎና የቦለቄ ዝርያዎች በአነስተኛ ቦታ በእጥፍ ምርት የሚሰጡ፣ ድርቅና በሽታን የሚቋቋሙ እና በአጭር ጊዜ የሚደርሱ በመሆናቸው ውጤታማ እንዳደረጋቸው ገልጸዋል ።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሰብል ምርጥ ዘር ድርጅት የዘር ብዜት እና ጥራት ማረጋገጥ ሥራ ክፍል ኃላፊ መሪነህ ታምሩ በክልሉ የምርጥ ዘር አቅርቦትን በራስ አቅም ለመሸፈን እየተደረገ ያለው ጥረት ውጤት እያመጣ መሆኑን ተናግረዋል።
የምርጥ ዘር ብዜት ስራው የአርሶ አደሩን ፍላጎት ያማከለ እና የአካባቢውን የአየር ሁኔታ ያገናዘበ መሆኑ ይበልጥ ውጤታማ እንዳደረጋቸውው ገልጸዋል።
በምርጥ ዘር ብዜቱ ትኩረት ከተደረገባቸው ሰብሎች በዋናነት በአጭር ጊዜ ምርት የሚሰጡና ድርቅን የሚቋቋሙ በመሆናቸው የአየር ንብረት ለውጥ ተፅእኖውን ለመቋቋም ያስችላሉ ብለዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምርጥ ዘር ድርጅት ዋና ሥራ አስኪጅ ብርሃኑ ግዛው በበኩላቸው የክልሉን የሰብል ምርጥ ዘር አቅርቦት ችግርን በራስ አቅም ለመፍታት እና ምርታማነት በእጥፍ ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ ነው
ለዚህም አርሶ አደሮችን፣ ማህበራትን እና የግል ባለሀብቶችን ያሳተፈ የምርጥ ዘር ብዜት ስራ በስፋት እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል።
የምርጥ ዘር ብዜት ስራው በክልሉ ሲያጋጥም የነበረውን የዘር አቅርቦት ችግር የቀረፈ ሲሆን አርሶ አደሩ እና በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶች እንደየ ፍላጎታቸው የተሻሻሉ ምርጥ ዘሮችን በበቂ ሁኔታ እንዲያገኙ አድርጓል ነው ያሉት።