የአዲስ አበባ ዘመናዊ ከተሜነት የዓለም ሕዝቦች የባህልና የኪነ-ጥበብ እሴታቸውን የሚያቀርቡባት የአፍሪካ የባህል ማዕከል እያደረጋት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባ ዘመናዊ ከተሜነት የዓለም ሕዝቦች የባህልና የኪነ-ጥበብ እሴታቸውን የሚያቀርቡባት የአፍሪካ የባህል ማዕከል እያደረጋት ነው
አዲስ አበባ፤ ህዳር 20/2019(ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ዘመናዊ የከተሜነት ግንባታ የዓለም ሕዝቦች የባህልና የኪነ-ጥበብ እሴታቸውን የሚያቀርቡባት የአፍሪካ የባህል ማዕከል እያደረጋት መሆኑን በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ሀፍታይ ገብረእግዚአብሔር ገለጹ።
የኢትዮ-ሩሲያ ባህላዊ ኪነ-ጥበብ ትርኢት ትናንት ምሽት በአዲስ አበባ ሕፃናት፣ ወጣቶች ቴአትር እና ሲኒማ ኮምፕሌክስ ተካሂዷል።
የአዲስ አበባ ቴአትርና ሲኒማ ቤቶች አስተዳደርና የዳንስ ቡድን ከሩሲያ ብሔራዊ የዳንስ ቡድን “ኮስትሮማ” ትናንት ምሽት በአዲስ አበባ ለመጀመሪያ ጊዜ ልዩ የጋራ የኪነ-ጥበብ ትርኢት አቅርበዋል።
በመርሃ ግብሩም የኢትዮጵያ ሀገር ፍቅር ባህላዊ የዳንስ ቡድን፣ የሩሲያ ብሔራዊ ባሌት ኮስትሮማ ዳንስ ቡድን፣ የተለያዩ ዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ፣ አርቲስቶችና የተለያዩ ሕብረተሰብ ክፍሎች ታድመዋል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ሀፍታይ ገብረእግዚአብሔር በዚህ ጊዜ እንዳሉት፤ መዲናዋ የዓለም ሕዝቦች የሐሳብና የባህል ልውውጥ የሚያደርጉባት የዲፕሎማሲ ማዕከል ናት።
የአዲስ አበባን ዘመናዊ ከተሜነት ከባህልና ኪነ-ጥበብ ባስተሳሰለ የመሰረተ ልማት ግንባታ በማስዋብ የአፍሪካ የጥበብ፣ የባህልና የፈጠራ ማዕከል እያደረጋት መሆኑን ገልጸዋል።
የኪነ-ጥበብ ባለሙያና ከያኒያን ልምድና ተሞክሯቸውን የሚጋሩበት ሰፋፊ መድረኮች መገንባታቸውንም አስረድተዋል።
የኢትዮ-ሩሲያ ባህላዊ የኪነ-ጥበብ ምሽትም የሕዝቦችን አብሮነትና ትስስር በማጠናከር የሀገራቱ ታሪካዊ ወዳጅነትና ትብብር የሚያሳይ መሆኑን አንስተዋል።
አዲስ አበባ ዘመናዊ የከተሜነት ግንባታ የዓለም ሕዝቦች ባህልና የኪነ-ጥበብ እሴታቸውን የሚያቀርቡባት የአፍሪካ የባህል ማዕከል እያደጋት መሆኑን አስረድተዋል።
በኢትዮጵያ የሩሲያ ፌዴሬሽን ኤምባሲ ጉዳይ አስፈጻሚ ሚካሂል ቦሮቭኮ በበኩላቸው፤ የኪነ-ጥበብ ዝግጅቶች የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቶችን የሚያጎለብቱ መድረኮች መሆናቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮ-ሩሲያ ባህላዊ የኪነ-ጥበብ ትርኢትም የሀገራቱን ታሪካዊ ሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት በማጠናከር ከፍተኛ አስተጽኦ የሚያበረክት የጋራ መድረክ መሆኑን ተናግረዋል።
የመድረኩ ታዳሚዎች መካከል ጽጌረዳ አድሐኖም፤ የኪነ-ጥበብ መድረኩ የኢትዮጵያን ባህላዊ እሴት ለዓለም ለማስተዋወቅ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው ብለዋል።
ሌላኛዋ ሩሲያዊት የመድረኩ ታዳሚ ሉድሚላ ዴኒሶቫ በበኩላቸው፤ የሀገራቱ የጋራ የኪነ-ጥበብ ምሽት የሕዝብ ለሕዝብ አብሮነትና ወዳጅነትን የሚያንጸባርቅ ማራኪ መድረክ ነው ብለዋል።
የኪነ-ጥበብ ትርኢቱ በኢትዮ-ሩሲያ መካከል የተገነባውን ታሪካዊ ወዳጅነት በማጠናከር የሀገራቱን ሕዝቦች ቱባ ባህላዊ እሴት ጎልቶ የታየበት አዝናኝ መድረክ ነው ያሉት ደግሞ አቶ ናትናኤል ሰለሞን ናቸው።