የትግራይ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ተመሠረተ - ኢዜአ አማርኛ
የትግራይ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ተመሠረተ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 20/2019 (ኢዜአ)፦ የትግራይ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ተወካዮች እንዲሁም በክልሉ የሚንቀሳቀሱ 19 የፖለቲካ ፓርቲዎች በተገኙበት በይፋ ተመሥርቷል።
በምሥረታ መድረኩ ላይ የአምስት ፓርቲዎች አመራሮች የምክር ቤቱ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሆነው የተመረጡ ሲሆን፤ በዚህም መሠረት፦
አቶ ዓምዶም ገብረሥላሴ – ሰብሳቢ
አቶ ብርሃነ ገብረጻድቅ – ምክትል ሰብሳቢ
አቶ ከበደ አሰፋ – ጸሐፊ
አቶ ሀፍቱ ኪሮስ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል
አቶ ጉዕሽ ጊደይ – የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ሆነው ተመርጠዋል።
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን አየለ በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ የትግራይ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት መመሥረት የፖለቲካ ኃይሎች ልዩነቶቻቸውን በሠለጠነ መንገድ እና በውይይት እንዲፈቱ ትልቅ እገዛ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች የርዕዮተ ዓለም ልዩነት ቢኖራቸውም በሀገር ሉዓላዊነት፣ በዘላቂ ሰላም፣ በብሔራዊ ጥቅም፣ በመቻቻል እና በመልሶ ግንባታ ጉዳዮች ላይ በጋራ እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል።
አክለውም በትግራይ የሚካሄደው ምርጫ ሰላማዊ እና ተአማኒ እንዲሆን እንዲሁም ተፈናቃይ ወገኖች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ቅድሚያ ተሰጥቶት እንዲሠራ አሳስበዋል። ብሔራዊው የጋራ ምክር ቤት ለትግራይ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አስፈላጊውን ተቋማዊ ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ነዋይ በበኩላቸው፣ ለመጪው ጠቅላላ ምርጫ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።
አዲሱ ምክር ቤት የምርጫ ሕጎችን እና ነጻነቱን ጠብቆ በመንቀሳቀስ የምርጫ ሥነ ምግባርን እንዲያከብር፣ በዴሞክራሲ እና በሰብአዊ መብቶች ዙሪያ እንዲመካከር እንዲሁም በፓርቲዎች መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በውይይት እንዲፈታ እንደሚጠበቅበት አመልክተዋል።
ምርጫ ቦርድ በትግራይ ክልል ነጻ፣ ገለልተኛ፣ ሙያዊ እና አካታች የሆነ ጠቅላላ ምርጫ ለማካሄድ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን የገለጹት አቶ ተስፋዬ፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እና ከመገናኛ ብዙኃን ጋር ተከታታይ ውይይቶች እንደሚደረጉ አረጋግጠዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች በመተዳደሪያ ደንባቸው መሠረት ዕጩዎችን እንዲመለምሉ እና ሕዝቡን ለምርጫ እንዲያዘጋጁ ሰብሳቢው ጠይቀዋል።