ቀጥታ፡

በልዩነቶች ውስጥ ያለውን አንድነት በማጠናከር ለዘላቂ ሰላምና አንድነት በጋራ መትጋት ይገባል

ቦንጋ፤ ሕዳር 20/2019 (ኢዜአ)፦‎ በልዩነቶች ዉስጥ ያለውን አንድነት በማጠናከር ለዘላቂ ሰላምና አንድነት በጋራ መትጋት እንደሚገባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ብሔረሰቦች ምክርቤት አፈ ጉባዔ አቶ  ዳንኤል ያዙ ገለፁ።

"ዘላቂ ሰላምና ልማት ለሕዝቦች ጠንካራ አንድነት" በሚል መሪ ቃል አጎራባች ክልሎችን ያሳተፈ የሕዝብ ለሕዝብ የምክክር መድረክ በቦንጋ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።

‎በምክክር መድረኩ ላይ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች፣ ከኦሮሚያ፣ ከጋምቤላ፣ ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ እና ከደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልሎች የተወጣጡ ተወካዮች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ብሔረሰቦች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ዳንኤል ያዙ፣ መድረኩ በብዝኃነት ውስጥ ያለውን ወንድማማችነትና ኅብረ-ብሔራዊ አንድነት ይበልጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።

ዘላቂ ሰላምና ልማትን ማረጋገጥ የሕዝቦችን ጠንካራ አንድነት የሚያጎለብት ከመሆኑም ባሻገር፣ ከዛሬ አልፎ የመጪውን ትውልድ ጥያቄ የሚመልስ ወሳኝ ጉዳይ ነው ብለዋል።

ሰላም በሌለበት ልማትን፣ ልማት በሌለበት ደግሞ ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ የማይታሰብ በመሆኑ፣ ሁሉም ለጋራ ውጤት በትብብር መሥራት እንደሚገባውም አቶ ዳንኤል ያዙ አጽንኦት ሰጥተዋል።

አጎራባች ክልሎችን የሚያስተሳስሩ ማኅበራዊና ባህላዊ እሴቶች ሊጠበቁ የሚገባቸው የጋራ ሀብቶቻችን ናቸው ያሉት አቶ ዳንኤል፤ ዘላቂ ሰላምን ለማጽናት በሕዝቦች መካከል የመተማመን ባህልን መገንባትና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ማጠናከር እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

በሂደቱም የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች እንዲሁም የተለያዩ ማኅበራዊ አደረጃጀቶች ያላቸውን ወሳኝ ሚና ይበልጥ ማጉላት እንደሚገባ ገልጸዋል።

የወሰን አካባቢዎች የግጭት ቀጣና ከመሆን ይልቅ የልማት፣ የንግድና የማኅበራዊ ትስስር ማዕከል እንዲሆኑ፣ የሚከሰቱ ችግሮችን በቅርበት እየተከታተለ ሰላማዊና ሕጋዊ እልባት የሚሰጥ የጋራ ትብብር ሥርዓት መዘርጋት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

በአካባቢዎቹ የመንገድ፣ የትምህርት፣ የጤና እና የንጹሕ መጠጥ ውኃ መሠረተ ልማቶችን በጋራ አቅዶ መሥራትና ያሉትን ጸጋዎች በትብብር መጠቀም እንደሚገባ አፈ-ጉባኤው አቶ ዳንኤል አሳስበዋል።

አንድነት ማለት ልዩነቶቻችንን አክብሮ ለጋራ ዓላማ መቆም ነው ያሉት አፈ-ጉባኤው፣ ጠንካራ አንድነት የሚገነባው በመተማመን፣ በፍትሐዊነትና በመከባበር እንዲሁም የጋራ ጥቅም ሲከበር መሆኑን ገልጸዋል።

ይህ መድረክ አዲስ የትስስር ምዕራፍ የሚከፈትበት፣ መተማመን የሚጎለብትበት እንዲሁም ከዚህ ቀደም የተጀመሩ ሥራዎች ይበልጥ የሚጠናከሩበት በመሆኑ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባም አሳስበዋል።

በመድረኩ መልዕክት ያስተላለፉት የካፋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ደመላሽ ንጉሴ፣ የካፋ ዞን በርካታ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በፍቅርና በአንድነት ተቻችለውና ተጋምደው የሚኖሩበት መሆኑን ገልጸዋል።

የሕዝብ ለሕዝብ ውይይቶችንና ምክክሮችን በማጠናከር የሕዝቦችን ወንድማማችነትና እህትማማችነት ማጎልበት፣ በጋራ ለማደግ ጠንካራ መሠረት የሚጥል መሆኑንም አንስተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም