የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ በታሪክ፣ በመልክዓ ምድርና በፍትሃዊ የልማት መርህ ላይ የተመሰረተ ወቅታዊ ጉዳይ ነው - ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ በታሪክ፣ በመልክዓ ምድርና በፍትሃዊ የልማት መርህ ላይ የተመሰረተ ወቅታዊ ጉዳይ ነው - ምሁራን
ወላይታ ሶዶ፤ ህዳር 20/2019 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ በታሪካዊ ዳራዋና በመልክዓ ምድራዊ አቀማመጧ ሲመዘን ትክክለኛና ፍትሐዊ ምላሽ የሚሻ መሆኑን የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን አስገነዘቡ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ የኢትዮጰያ የባሕር በር ጥያቄ ከሉዓላዊነትና ከሀገር ደህንነት ጋር የሚገናኝ መሆኑን ማንሳታቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ተደራሽነትን በሰላማዊ መንገድና በድርድር ለማግኘት የሚደረገው ጥያቄ አዲስ ነገር አለመሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ዮርዳኖስና ሳዑዲ ዓረቢያ፣ ኢራቅና ኢራን እንዲሁም ፖላንድ የባህር በር ያገኙበትን አካሄድ አስረድተዋል።
በማበራሪያቸውም ኢትዮጵያ በሰማይም ይሁን በምድር ተዘግታ መኖር እንደማትችል አስረግጠዋል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስ እና ስነ-ሰብ ኮሌጅ የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ፕሮፌሰር ንጋቱ አበበ (ዶ/ር) በሰጡት ማብራሪያ፣ የባህር በር ሀገራት የንግድ ትስስራቸውን የሚያሳልጡበትና ህልውናቸውን የሚያፀኑበት መሠረታዊ የኢኮኖሚ ምሰሶ መሆኑን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ላለፉት በርካታ ዘመናት ሉዓላዊነቷን አስጠብቃ የባህር በር ስትጠቀም ብትቆይም በመሐል በተፈጠረ የታሪክ ስህተት ፍትሃዊ ባልሆነ መንገድ የባህር በር ማጣቷ የሚያስቆጭ ነው ብለዋል።
ቢሆንም በአሁኑ ወቅት በተፈጠረው ታሪካዊና ፍትሐዊ የልማት መነሻነት የባህር በር የማግኘት መብቷን ማረጋገጥ አስፈላጊ በመሆኑ አለም አቀፍ ሀገራትም ለዚህ የኢትዮጵያ ፍትሐዊ ጥያቄ ተገቢውን ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ዓለም አቀፍ ግንኙነት በሀገራት ተፅዕኖ ፈጣሪነት አቅም የሚቃኝ መሆኑን የገለጹት ምሁሩ፣ ኢትዮጵያ በተለያዩ መስኮች እያሳደገች ያለችው ሁለንተናዊ አቅም በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ጉልህ ተጽዕኖ የመፍጠር ዕድል እንደሚሰጣት አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ ይህንን አቅሟን በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብና በአባይ ወንዝ ላይ በተግባር ማረጋገጧን ጠቅሰው፣ ይህንኑ ስኬትና ድል ለሰፊውና ወሳኝ ለሆነው የባህር በር ጥያቄ መሳካት ልትጠቀምበት ይገባል ብለዋል።
የኢትዮጵያና የባህር በር ለረዥም ዘመናት የዘለቀ የማይነጣጠል ታሪካዊ ቁርኝት እንዳላቸው የተናገሩት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የታሪክ እና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ጳውሎስ ባልቻ ናቸው።
ቢሆንም ሀገራችን ያለ ምንም ውይይትና የህዝብ ውሳኔ ከቀይ ባህር እንድትርቅና የባህር በር እንድታጣ የተሴረባት ሴራና ሸፍጥ ሀገሪቱ በቀጠናው ያላትን የበላይነት ከማደናቀፍ ባሻገር በወደብ ኪራይ በርካታ ወጪ እንድታወጣ በማድረግ ለኢኮኖሚያዊ ቀውስ መዳረጉን ተናግረዋል።
አሁን መንግስት የባህር በር ዳግም ለማስመለስ የጀመረው ጥረትም አዲስ ነገር ሳይህን በታሪክም ሆነ በጂኦፖለቲካዊ እውነታዎች ትክክለኛ እና የመኖር ያለመኖር የህልውና ጉዳይ መሆኑን ነው የገለጹት።
የአባይና የቀይ ባህር የውሃ አካላት ለረጅም ዓመታት የሀያላን ሀገራት የስበት ማዕከል ሆነው መቆየታቸውን ጠቅሰው፤ የባህር በር ጉዳይ እውን መሆን ለቀጠናው ሀገራት ትስስርና የጋራ ልማት ድርሻው የጎላ መሆኑን ተናግዋል።
ኢትዮጵያ በቀጠናው ይነሳ የነበረውን የባዕዳንን ሴራና ፈተናዎችን በታሪካዊና ህልውናዊ ጥንካሬ ተቋቁማ ያለፈችበትን እንዲሁም በህዳሴ ግድብ ያሳየችውን ጥንካሬ ለመድገም የጀመረችው ጥረት የሚደነቅ መሆኑንም ምሁሩ አንስተዋል።