ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር ኃይል የሀገራችንን ዳር ድንበርና የአየር ክልል እያስጠበቀ በልማት ስራዎች ላይም ከፊት ሆኖ እየሰራ ይገኛል -ሌተናል ጀነራል ይልማ መርዳሳ

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 20/2019(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር ኃይል የሀገራችንን ዳር ድንበርና የአየር ክልል እያስጠበቀ በልማት ስራዎች ላይም ከፊት ሆኖ እየሰራ እንደሚገኝ የአየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል ይልማ መርዳሳ ገለጹ።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል 91ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን በማሥመልከት ቢሾፍቱ ከተማ ያዘጋጀው የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ በወንዶች ቢኒያም መላክ ፤ በሴቶች ደግሞ አዳኑ ሄንቆ አሸናፊ በመሆን ተጠናቋል።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል ይልማ መርዳሳ ለውድድሩ አሸናፊዎች እንኳን ደስ አላችሁ በማለት የአየር ኃይልን የ91ኛ ዓመት የድል ጉዞ በማሰብ በተደረገው ጥሪ የመጣችሁ በሙሉ እናመሰግናለን ብለዋል።

አዛዡ አየር ሀይል የሀገራችንን ዳር ድንበርና የአየር ክልል እያስጠበቀ የቢሾፍቱ ከተማ ሁሉ አቀፍ የልማት ስራዎች ላይም ከፊት ሆኖ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው ይህንን ታሪካዊ በአል ከህብረተቡ ጋር ማክበር ትልቅ ትርጉም እንዳለውም ገልፀዋል።

የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ መኪዮ መሀመድ በበኩላቸው በኢትዮጵያ የስፖርት ታሪክ የጀመረው ከፀጥታ ተቋማት መሆኑን አስታውሰዋል።

91 ዓመታትን ያስቆጠረው አየር ኃይል ይህን ታሪክ ለማስቀጠል እየሰራ ያለና ወንድማማችነትን ለማጠናከር ትልቁን ድርሻ እየተወጣ የስፖርት ዘርፍን እየደገፈ ይገኛል ብለዋል።

በውድድሩ በወንዶች ቢኒያም መላክ ከሸገር ሲቲ 1ኛ ደረጃን በመያዝ የወርቅ ሜዳሊያና የ500 ሺህ ብር እንዲሁም በሴቶች አዳኑ ሄንቆ ከሸገር ሲቲ 500 ሺህ ብርና የወርቅ መዳሊያ ተሸላሚ ሆነዋል።

በወንዶች 2ኛ ሙሲን ሀጂ ከሸገር ሲቲ 3ኛ ጭንቢሳ ደበሌ ከሸገር ሲቲ አሸናፊ ሲሆኑ በሴቶች 2ኛ ቢቄሌ አንበሶ ከኦሮሚያ ፓሊስ 3ኛ ቤቴሊሄም አለና ከሸገር ሲቲ አሸናፊ በመሆን 2ኛ ደረጃ የያዙ የ250 ሺህ ብር 3ኛ ደረጃ የያዙ የ150 ሺህ ብር ተሸላሚ ሆነዋል።

የውድድሩ አሸናፊዎች አየር ኃይል ባዘጋጀው የጎዳና ላይ ሩጫ ማሸነፋቸው የፈጠረባቸው ደስታ የተለየ መሆኑን ጠቅሰው "አየር ኋይል መመኪያችን" ነው ሲሉም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም