ቀጥታ፡

የአፍሪካ ሀገራት የሕዝብ ጤና ኢንቨስትመንትን በማስፋት ራስ የመቻል ሽግግርን ማፋጠን አለባቸው - አቡባክሪ ዲያው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 20/2019(ኢዜአ)፦ የአፍሪካ ሀገራት የሕዝብ ጤና ጥበቃ ኢንቨስትመንትን በማስፋት ራስ የመቻል ሽግግርን ማፋጠን እንዳለባቸው በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የጽሕፈት ቤትና የዘላቂ የጤና ፋይናንስ ፕሮጀክት መሪ አቡባክሪ ዲያው ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከኅዳር 14 እስከ 18 ቀን 2019 ዓ.ም ድረስ የሚቆየውን 5ኛው ዓለም አቀፍ የአፍሪካ የሕዝብ ጤና ጉባኤ (CPHIA 2026) መክፈታቸው ይታወሳል።

ጉባኤውም “የአፍሪካ የጤና ደኅንነትና ሉዓላዊነት፤ ከጤና ጥገኝነትና ተጋላጭነት ወደ ባለቤትነትና ጽናት የሚደረግ ሽግግር” በሚል መሪ ሐሳብ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል በታላቅ ስኬት ተካሂዷል።

በአፍሪካ የበሽታዎች መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከልና በኢትዮጵያ መንግሥት ትብብር በተዘጋጀው ጉባኤ ከ100 በላይ ሀገራት የተውጣጡ ከ30 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች ታድመዋል።

በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የጽሕፈት ቤትና የዘላቂ የጤና ፋይናንስ ፕሮጀክት መሪ አቡባክሪ ዲያው ለኢዜአ እንዳሉት፣ የጤና ዘርፍ የልማት አጋሮች ድጋፍ እየቀነሰ መጥቷል።

በዚህም የአፍሪካ ሀገራት የመንግሥትን በጀት ከግሉ ዘርፍ ኢንቨስትመንትና ተሳትፎ ጋር በማስተሳሰር የአህጉሪቷን የጤና ሥርዓት አቅም የሚያጎለብት የፋይናንስ አማራጮችን ማጠናከር አለባቸው ብለዋል።

ሀገራቱም የውስጥ አቅምን ከልማት አጋሮች ድጋፍ ጋር በማሰናሰልና የሕዝብ ጤና ጥበቃ ኢንቨስትመንትን በማስፋት ራስ የመቻል ሽግግርን ማፋጠን እንዳለባቸው አስረድተዋል።

የአፍሪካውያንን ከፍተኛ ቁጥር ታሳቢ በማድረግም ብሔራዊ የጤና መድን ሥርዓት ተደራሽነትን በማስፋት ለሕዝብ ጤና ቅርብ የሆነ አገልግሎት መፍጠር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

የአፍሪካን የጤና መድን ሥርዓትም የመክፈል አቅም የሌላቸውና አቅመ ደካማ ዜጎችን የጤና አገልግሎት ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ መሆን እንደሚጠበቅበት አስገንዝበዋል።

የመንግሥታቱ ድርጅት የልማት አጋሮችም የአፍሪካ ሀገራት ትብብራቸውን በማጎልበት ለዜጎች የጤና ሥርዓት ውጤታማነት ድጋፍ እያደረጉ ነው ብለዋል።

ጤና እንደ ማኅበራዊ ወጪ ሳይሆን እንደ ኢንቨስትመንት መታየት አለበት የሚለውን አስተሳሰብ በመፈክር ብቻ ሳይሆን በማስረጃና በዝርዝር ትንታኔ ማረጋገጥ እንደሚገባ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም