የአዳማ ሣይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ራስ ገዝ ለመሆን የሚያስችለውን ቅድመ ዝግጅት አጠናቀቀ - ኢዜአ አማርኛ
የአዳማ ሣይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ራስ ገዝ ለመሆን የሚያስችለውን ቅድመ ዝግጅት አጠናቀቀ
አዳማ፤ ህዳር 20 /2019 (ኢዜአ)፡- የአዳማ ሣይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ራስ ገዝ ለመሆን የሚያስፈልጉ የቅድመ ዝግጅት ተግባራት ማጠናቀቁን ገለጸ።
መንግስት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአካዳሚክ ነጻነታቸው ተረጋግጦ የመማር ማስተማር፣ የምርምር እና የማህበረሰብ አገልግሎት ሥራዎቻቸውን በብቃት እንዲያከናውኑ ለማስቻል የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ አዋጅን አውጥቶ ተግባራዊ ማድረግ ጀምሯል።
አዋጁም ለሀገር ዘላቂ ዕድገትና ብልጽግና ወሳኝ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ፤ በቴክኖሎጂ፣ በፈጠራና በችግር ፈቺ ምርምሮች የላቀ እውቀትና ክህሎት ያለው ብቁ የሰው ኃይል የሚያፈሩ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ለመገንባት ያለመ ነው።
በዚሁ መሠረት የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲም ወደ ራስ ገዝነት ለመሸጋገር የሚያስችለውን ዝግጅት ማገባደዱን ነው የገለጸው።
የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ያደሳ መላኩ ለኢዜአ እንዳስታወቁት የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ስርዓትን ተግባራዊ ለማድረግ ቅድመ ዝግጅት አጠናቋል።
በዚህ ረገድ የትምህርት ሚኒስቴር ያወጣውን መስፈርቶችና መመዘኛዎች መሠረት ያደረገ በቂ ዝግጅት ሲያደረግ ቆይቷል ብለዋል።
ለዚህም ዩኒቨርሲቲው ያለውን ሀብት የመለየት፣ ያሉበትን ክፍተቶች በሚገባ የመገምገምና የመፈተሽ፤ ተቋማዊ ግምገማ ሠነድ፣ ስትራቴጂክ እቅድ፣ ፖሊሲና መመሪያዎችን ጨምሮ 54 የሚሆኑ ዶክመንቶች የማዘጋጀት ስራዎቹን አጠናቋል ብለዋል።
በዶክመንቶቹ ዝግጅት ሂደት የዩኒቨርሰቲውን መምህራንና ተማሪዎች እንዲሁም ባለድርሻ አካላትን በማማከር ሰነዶቹ እንዲዳብሩ መደረጉን አስረድተዋል።
የተዘጋጁ ሠነዶቹንም ለትምህርት ሚኒስቴር በማቅረብ እና በማስገምገም ዩኒቨርሲቲው ግብረ መልስ ማግኘቱን ፕሮፌሰር ያደሳ አስታውቀዋል።
ይህንኑ ተከትሎ ዩኒቨርሲቲው በአጭር ጊዜ ውሰጥ በሀገር አቀፍ ደረጃ ራስ ገዝ እንዲሆኑ ከተመረጡ ጠዘኝ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቀጥሎ 2ኛ እንደሚሆን ፕሮፌሰሩ አረጋግጠዋል።
ዩኒቨርሲቲው ራስ ገዝ ሆኖ አካዳሚያዊ እና አስተዳደራዊ ነፃነቱ ተጠብቆ መንቀሳቅስ እንዲችል በትምህርት ዘርፍ ለተጀመረው ሪፎርም ስኬታማነት ፈር ቀዳጅ ተግባሩን አጠናክሮ መቀጠሉን ከፕሮፌሰር ያደሳ ገለፃ ለመረዳት ተችሏል።
ዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር፣ የምርምር እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ስራዎችን ውጤታማ ለማድረግ የመሰረተ ልማት ግንባታ ላይም ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ቀደም ሲል ኢዜአ መዘገቡ ይታወሳል።
በተለይም በዩኒቨርሲቲው የምርምር ፓርክ ውስጥ ለሚገኙ አምስት የልህቀት ማዕከላት 30 ቤተ ሙከራዎችን የማደራጀት ስራም እየተፋጠነ መሆኑ እንዲሁ።
ይህ ፓርክ ከዩኒቨርሲቲው ባሻገር እንደ ሀገር በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዘርፎች ግዙፍ እና ልዩ የምርምር ማዕከል በመሆን የላቀ ፋይዳ እንደሚኖረው ተመላክቷል።