ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ እያከናወነች ያለችው ተግባር ለዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው - ምሁራን

አርባምንጭ፤ ህዳር 20/2019 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር እያከናወነች ያለችው ሥራ ለዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን የዘርፉ ምሁራን ገለጹ።

የአየር ንብረት ለውጥ የዓለም አቀፍ ዋነኛ ፈተና ሆኖ በቀጠለበት በዚህ ወቅት፣ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር እያከናወነች ያለችው ሥራ ለሀገራዊ ልማት ብቻ ሳይሆን ለዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።

አረንጓዴ አሻራ ከችግኝ ተከላ በላይ የተፈጥሮ ሀብትን የማደስ፣ የደን ሽፋንን የማሳደግ፣ የውሃ ሀብትን የማጎልበትና ለትውልድ የሚሻገር የአካባቢ ጥበቃ ባህልን የመገንባት ባህል ሆኗል።

በመደመር እሳቤ የሚከናወነው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አህጉራዊ ብቻ ሳይሆን አለምአቀፋዊ ተጽእኖ መፍጠር ያስቻለና ለሌሎችም ምሳሌ መሆን የሚችል ተግባር መሆኑ እየተነገረለት ይገኛል።

የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ምሁራንም የአረንጓዴ አሻራ በሀገሪቱ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና የውሃ አቅም መጨመር ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በዩኒቨርሲቲው የግብርና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን፣ የዕፅዋት ሳይንስ መምህርና ተመራማሪ ደግፌ አሰፋ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም በወሰደችው እርምጃ ተጨባጭ ውጤቶችን እያስመዘገበች ትገኛለች።

ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ ለዓለም ምሳሌ የሚሆን ተግባር በመፈጸሟ 32ኛውን የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 32) አዘጋጅ ሆና እንድትመረጥ አስችሏታል ብለዋል።

አረንጓዴ አሻራ የኢትዮጵያ የዛሬ የልማት ጥረት ብቻ ሳይሆን ለመጪው ትውልድና ለዓለም የተፈጥሮ ሚዛን የሚተላለፍ የጋራ ትሩፋት መሆኑንም ጠቁመዋል።

በተለይም የከርሰ ምድርና የገጸ ምድር ውሃ ሀብት እንዲጎለብት በማገዝ፣ ለግብርና ምርታማነትና ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ የራሱን ድርሻ እያበረከተ መሆኑን አመልክተዋል።

አረንጓዴ አሻራ ከአካባቢ ጥበቃ ባሻገር ለስነ-ምግብ፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ለገቢ ምንጭ መስፋፋትና ለኢኮኖሚ ሉዓላዊነት መጎልበትም ወሳኝ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በዓለም የኢንዱስትሪ መስፋፋትና የነዳጅ አጠቃቀም መጨመር ምክንያት የሚከሰተውን የካርቦን ልቀት ለመቀነስም የደን ሀብትን ማሳደግ ወሳኝ መፍትሔ እንደሆነ አስገንዝበዋል። 

በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ የጀመረችው ሰፊ የአረንጓዴ ልማት ንቅናቄ ሌሎች ሀገራትም ሊማሩበት የሚችል ተሞክሮ መሆኑን አንስተዋል።

በዩኒቨርሲቲው የተፈጥሮ ሀብት አያያዝ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ዋቅሹም ሽፈራው (ዶ/ር) በበኩላቸው ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ ያስመዘገበችው ውጤት ለዓለም አቀፍ የአካባቢ ጥበቃ ጥረት ተምሳሌታዊ ነው ብለዋል።

የተፈጥሮ ሀብት የዛሬ ትውልድ ብቻ የሚጠቀምበት ሳይሆን ከመጪው ትውልድ የተበደርነው ሀብት በመሆኑ በአግባቡ መጠበቅና ማልማት የሁሉም ዜጋና ኃላፊነት መሆኑንም አስገንዝበዋል።

እንደ ምሁሩ ገለጻ፣ የአየር ንብረት ለውጥ የአንድ ሀገር ችግር ብቻ  ሳይሆን ድንበር የማይገድበው ዓለም አቀፋዊ ፈተና በመሆኑ የሁሉም ሀገራት ትብብርና የጋራ ኃላፊነት እንደሚጠይቅ አመላክተዋል።

ኢትዮጵያ ባለፉት ተከታታይ ዓመታት በቢሊዮን የሚቆጠሩ  ችግኞችን መትከሏ ለአረንጓዴ ልማት ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ታላቅ ርብርብ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ አበርክቶ በሀገር ውስጥ የደን ሀብትንና የውሃ ምንጮችን ከማሳደግ ባሻገር፣ የካርቦን ልቀትን ለመቀነስ፣ የብዝሃ ሕይወትን ለመጠበቅና የዓለምን የአካባቢ ጤና ለማሻሻል የሚያግዝ አበርክቶ ነው ብለዋል።

ምሁራኑ ኢትዮጵያ የጀመረችው የአረንጓዴ ልማት ጥረት ዘላቂ ውጤት እንዲያስገኝ የተተከሉ ችግኞችን በመንከባከብና ሌሎች ሀገራት እንድሳተፉ በማድረግ የአከባቢ ጥበቃን ማጠናከር እንደሚገባ ጠቁመዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም