ቀጥታ፡

በሲዳማ ክልል እስካሁን 168 ሺህ ቶን ቡና ተሰብስቧል

ሀዋሳ፤ ህዳር 20/2019(ኢዜአ)፡- በሲዳማ ክልል በተያዘው ምርት ዘመን እስካሁን 168 ሺህ ቶን እሸት ቡና መሰብሰቡን የክልሉ ቡና ፣ ፍራፍሬና ቅመማ ቅመም ባለሥልጣን ገለፀ፡፡

የሲዳማ ክልል ቡና፣ ፍራፍሬና ቅመማ ቅመም ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ታሪኩ ዶንቃ እንደገለጹት፣ በክልሉ በዘንድሮው የምርት ዘመን 198 ሺህ ቶን ቡና ለመሰብሰብ  እና ከዚህ ውስጥ 35 ሺህ ቶን ታጥቦ የተቀሸረ እሸት ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ታቅዶ እየተሠራ ነው።
 


እስካሁን 168 ሺህ ቶን ቡና ጥራቱን ጠብቆ እንዲሰበሰብ ማድረግ መቻሉን ገልጸው፣ በቀሪ ጊዜያት በሚሰበሰብ ምርት ዕቅዱን ሙሉ በሙሉ ማሳካት የሚያስችል ሁኔታ መኖሩን ጠቁመዋል።

የምርት መሰብሰብ ሥራው ባልተጠናቀቀባቸው ደጋማና ወይና ደጋ አካባቢዎች አሁንም በላኪ አርሶ አደሮች፣ በግል ባለሀብቶች፣ በማኅበራትና በአክሲዮን ድርጅቶች አማካይነት ሥራው ተጠናክሮ መቀጠሉን አውስተዋል።

የቡና ጥራትን የማስጠበቅ ሥራ ከዘር መረጣና ከማሳ እንክብካቤ ጀምሮ እስከ ምርት መሰብሰብ ሂደት ድረስ ጠንካራ ክትትልና ድጋፍ የሚደረግበት እንደሆነ አቶ ታሪኩ አስረድተዋል።

ከክልሉ ለማዕከላዊ ገበያ ከቀረበው ቡና ውስጥ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው አንደኛ ደረጃን የያዘ መሆኑንም አብራርተዋል።

በክልሉ ዳሌ ወረዳ በዘርፉ የተሰማሩት አርሶ አደር አፊራ ገቢባ፣ ጥራት ያለው ምርት ለመሰብሰብ የቡና ልማት ሥራቸውን ከችግኝ ማፍላት ጀምሮ በጥንቃቄ እንደሚያከናውኑ ተናግረዋል።

ምርጥ ዘር የመምረጥ፣ በጥንቃቄ ችግኝ የማፍላት፣ በባለሙያ እገዛ ለተከላ የሚሆን ጉድጓድ የመቆፈርና በተፈጥሮ ማዳበሪያ የማልማት ሥራ እያከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

ከተከላ በኋላም ማሳቸውን ከመንከባከብ ባለፈ፣ ምርቱ ሲደርስ የብስለት ደረጃውን ጠብቆ የመልቀምና የማዘጋጀት ሥራን በተገቢው መንገድ እንደሚያከናውኑ አስረድተዋል።

በጥራት ያዘጋጁትን ቡና የእርጥበት (የድርቀት) መጠኑን በባለሙያ አስፈትሸው ወደ መጋዘን እንደሚያስገቡ የተናገሩት አርሶ አደር አፊራ፣ በአሁኑ ወቅት 92 ኩንታል ተቀሽሮ ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ቡና ማዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

የዚሁ ወረዳ ቡና ላኪ አርሶ አደር ፍቃዱ ፊታሞ በበኩላቸው፣ ከማሳቸው 300 ኩንታል እሸት ቡና መሰብሰባቸውን ጠቅሰው፣ እስካሁን 160 ኩንታል ተቀሽሮ ለውጭ ገበያ የሚውል ቡና ማዘጋጀታቸውን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም