ቀጥታ፡

ነገሌ አርሲ ከሲዳማ ቡና የሚያደርጉት የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 20/2019 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሰባተኛ ሳምንት የሶስተኛ ቀን ውሎ አራት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
 
የሊጉ መሪ ነገሌ አርሲ ከወቅቱ ሻምፒዮን ሲዳማ ቡና በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ምሽት 12 ላይ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።

ነገሌ አርሲ በ14 ነጥብ ሊጉን እየመራ ነው።  ሲዳማ ቡና በአራት ነጥብ 15ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።

ነገሌ አርሲ በሊጉ እስከ አሁን ባደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች በአራቱ ድል ሲቀናው ሁለት ጊዜ አቻ ወጥቷል።

በጨዋታዎቹ ላይ ስምንት ግቦችን ሲያስቆጥር ሁለት ጎሎችን አስተናግዷል።

ተጋጣሚው ሲዳማ ቡና በሊጉ ባደረጋቸው ሶስት ጨዋታዎች በአንዱ ሲያሸንንፍ አንድ ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል።

በቀሪው ጨዋታ ነጥብ ተጋርቷል።  በነዚህ ጨዋታዎች ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር በተመሳሳይ ሁለት ጎሎች ተቆጥረውበታል።

የወቅቱ ሻምፒዮን ሲዳማ ቡና በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ማጣሪያ ተሳትፎው ምክንያት ያላደረጋቸው ሶስት ተስተካካይ ጨዋታዎች አሉት።

ተስተካካይ መርሐ ግብሮቹ ክለቡ ከጋሞ ጨንቻ፣ ኢትዮጵያ መድን እና ሀዋሳ ከተማ ጋር የሚያደርጋቸው ናቸው።

ሁለቱ ክለቦች በ2018 ዓ.ም በሊጉ ባደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች ነገሌ አርሲ በአንዱ ድል ሲቀናው በቀሪው መርሐ ግብር አቻ ተለያይተዋል።

በመጀመሪያው ዙር መርሐ ግበር ነገሌ አርሲ በዳዊት ተፈራ የፍጹም ቅጣት ምት ጎል 1 ለ 0 አሸንፏል።

በሁለተኛው ዙር ሁለቱ ክለቦች አቻ ተለያይተዋል። ብርሃኑ በቀለ ለሲዳማ ቡና እና በረከት ወልዴ በፍጹም ቅጣት ምት ለነገሌ አርሲ ግቦቹን አስቆጥረዋል።

የአቻ ውጤቱን ተከትሎ ሲዳማ ቡና በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የሊጉን ዋንጫ ማንሳቱን  ማረጋገጡ አይዘነጋም።

ሁለቱ ክለቦች አምና በሊጉ ጠንካራ ፉክክር አድርገዋል።

ሲዳማ ቡና በ68 ነጥብ አንደኛ፣ ነገሌ አርሲ በ60 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል።

የእሁዱ ጨዋታ ጠንካራ እና አዝናኝ ፉክክር ይደረግበታል የሚል ሰፊ ግምት አግኝቷል።

የሁለቱ ክለቦች ደጋፊዎች  የሚያደርጉት ድጋፍ ለጨዋታው ደማቅ እና ማራኪ ድባብ ይሰጠዋል ተብሎ ይጠበቃል።

በዕለቱ ተጨማሪ ሶስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከወላይታ ድቻ ጋር ከቀኑ 9 ሰዓት ከ30 በአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታውን ያከናውናሉ።

አዳማ ከተማ ከሃዋሳ ከተማ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም፣ ከቀኑ 10 ሰዓት ባህር ዳር ከተማ ከመቻል በባህር ዳር ኢንተርናሽናል ስታዲየም ይጫወታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም