ቀጥታ፡

የኢትዮጵያና የደቡብ አፍሪካ ታሪካዊ ወዳጅነት በከፍተኛ ትምህርት ትብብር እየተጠናከረ ነው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 19/2019 (ኢዜአ)፦በፓን አፍሪካኒዝም መንፈስ የተመሠረተው የኢትዮጵያ እና የደቡብ አፍሪካ ታሪካዊ ወዳጅነት በከፍተኛ ትምህርት ትብብር ተጠናክሮ መቀጠሉን በኢትዮጵያ የደቡብ አፍሪካ አምባሳደር ኖንሴባ ሎሲ ገለጹ።

የደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን 61 ተማሪዎች በዛሬው ዕለት አስመርቋል።



 

ከተመራቂዎቹ መካከል 58ቱ የፒኤችዲ፣ ሁለቱ የማስተርስ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል። አንድ ደግሞ የክብር ዶክትሬት ተሸላሚ ናቸው።

በኢትዮጵያ የደቡብ አፍሪካ አምባሳደር ኖንሴባ ሎሲ ለተመራቂዎች የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

አምባሳደር ኖንሴባ ሎሲ እንደተናገሩት፤ የደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ በኢትዮጵያ ማስተማር ከጀመረ ሃያ ዓመታትን አስቆጥሯል።

በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ያሉት የርቀት ትምህርት መርሃ ግብሮች የሁለቱን ሀገራት የትምህርት ትስስር እያጠናከረ መሆኑን ገልጸው፤ በዚህም ለሀገርና ለአኅጉር ዕድገት አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ብቁ ምሁራንንና ተመራማሪዎችን እያፈራ መሆኑን አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ ከ1960ዎቹ የነፃነት ትግል አንስቶ ለኔልሰን ማንዴላ ባደረገችው ድጋፍ የጸናው የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ዛሬ ወደ ተለያዩ ዘርፎች ማደጉን ገልጸዋል።

በተለይም በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ የተፈረመው የመግባቢያ ሰነድ ለአካዳሚክ ልውውጥ፣ ለትብብር ምርምር እና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት መጠናከር ቁልፍ ሚና እያበረከተ መሆኑን አብራርተዋል።

የደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ የርቀት ትምህርት ተደራሽነትን በማስፋት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን የዶክትሬትና የድኅረ ምረቃ ተመራቂዎችን እያፈራ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህም የሁለቱ ሀገራት የከፍተኛ ትምህርት ትስስር እየተጠናከረ መምጣቱን እንደሚያሳይ ተናግረዋል።

የጤና ሚኒስቴር መሪ ሥራ አስፈጻሚ አሰግድ ሳሙዔል በምረቃ ሥነ ስርዓቱ ላይ፤ የመደመር እሳቤ እና ተቋማዊ ትብብር ለጋራ ብልፅግና ወሳኝ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ከደቡብ አፍሪካ መንግሥት እና ከደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ጋር ያላትን ቀጣይነት ያለው ትብብር ከፍ አድርጋ እንደምትመለከተው ገልጸዋል።

የመደመር ርዕይ አቅሞችን አቀናጅቶ ለጋራ ዕድገት ማዋልን እንደሚያመለክት ጠቅሰው፤ ተመራቂዎቹ ኢትዮጵያን እና አኅጉራቸውን በቅንነት እንዲያገለግሉ አስገንዝበዋል።

የደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ የተቋማዊ ልማትና ትራንስፎርሜሽን ምክትል ኃላፊ ፕሮፌሰር ሰለሞን ማጋኖ፤ ተመራቂዎች ያገኙትን እውቀትና ክህሎት በመጠቀም በአፍሪካ የሚስተዋሉ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ችግሮችን  ለመፍታት በግንባር ቀደምትነት መሥራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡

በተማሩባቸው የትምህርት መስኮች ማኅበረሰቡን ለማገልገል መዘጋጀታቸውን የተናገሩት ደግሞ የተመራቂ ተማሪዎች ተወካይ ሰለሞን አበባው (ዶ/ር) ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም