ቀጥታ፡

ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት ያላቸውን ሚና ማጠናከር አለባቸው

አርባ ምንጭ፤ ህዳር 19/2019 (ኢዜአ)፦ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የምርምር ውጤቶቻቸውን ወደተግባር በመቀየር ለሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት ያላቸውን ሚና ማጠናከር እንዳለባቸው ተገለጸ።

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ዓለም አቀፍ የሥራ ፈጠራ ሳምንትን በማስመልከት ከኢትዮጵያ የሥራ ፈጠራ ልማት ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ለአንድ ሳምንት ያዘጋጁት የሥራ ፈጠራ ሥልጠና ማጠቃለያ መድረክ ተካሂዷል።


 

የሥራ ፈጠራ ሳምንትን በማስመልከት ለአንድ ሳምንት በተሰጠው ስልጠናም ከአንድ ሺህ በላይ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች፣ መምህራንና የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አካላት መሳተፋቸው ተመላክቷል።

በማጠቃለያ መድረኩ የተገኙት የአርባ ምንጭ ከተማ ከንቲባ ኢንጂነር ሀብታሙ መለሰ (ዶ/ር) የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚና በመማር ማስተማር ብቻ ሳይወሰን በፈጠራ ቴክኖሎጂ ለኢኮኖሚ እድገት ያላቸው አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑን አንስተዋል።

ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ብቁ ዜጋ በማፍራት በኩል ወሳኝ ሚና እንዳለቸው ገልጸው፣ ተማሪዎቻቸው የተሟላ ዕውቀትና ክህሎት ያላቸው የመልካም ስብዕና ባለቤት ሆነው እንዲወጡም መትጋት አለባቸው ብለዋል።

ተማሪዎችም የመንግሥትና የግል ተቋማትን የሥራ ቅጥር ዕድል ብቻ ከመጠበቅ ይልቅ አዳዲስ የፈጠራ ውጤቶችን በማፍለቅና የራሳቸውን የሥራ ዕድል በመፍጠር ለሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት የድርሻቸውን እንዲወጡ አስገንዝበዋል።

ከተማ አስተዳደሩም ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በፈጠራ ቴክኖሎጂ፣ በሥራ ፈጠራና በኢኮኖሚ ሽግግር ዙሪያ በትብብር እንደሚሠራም አረጋግጠዋል።


 

የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ቦጋለ ገብረማሪያም (ዶ/ር) በበኩላቸው እንዳሉት፣ ዩኒቨርሲቲውን የፈጠራና የዕውቀት ልህቀት ማዕከል ለማድረግ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።

ተማሪዎች በትምህርት ያገኙትን ዕውቀትና ክህሎት ተጠቅመው በየአካባቢው ያሉ የተፈጥሮ ፀጋዎችን ወደ ሀብት ምንጭነት በመቀየር በሀገር ሁለንተናዊ እድገት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም አሳስበዋል።

ዩኒቨርሲቲው ከባለድርሻ አካላት ጋር ትስስር በመፍጠር ለህብረተሰቡ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መፍትሄ የሚሆኑ የምርምር ውጤቶችን ለማፍለቅ እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።


 

በዩኒቨርሲቲው የኢንተርፕርነርሺፕ ልማትና ቴክኖሎጂ ማበልጸጊያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አብዮት ፀጋዬ (ዶ/ር) የፈጠራ ሐሳብ የሚያፈልቁ ዜጎችን ለማፍራትና የሥራ ፈጠራ ባህልን ለማሳደግ ትኩረት መሰጠቱን አንስተዋል።

ከሥልጠና የሚፈልቁ የፈጠራ ሥራዎች በሐሳብ ብቻ እንዳይቀሩ ወደ ተጨባጭ ምርትና አገልግሎት እንዲቀየሩ መንግሥት ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።


 

ከሥልጠናው ተሳታፊዎች መካከል በዩኒቨርሲቲው የሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ አምስተኛ ዓመት ተማሪዎች ቀነኒሳ ሚሶ እና ወንድማገኝ ታደሰ በፈጠራ ክህሎታቸው ሁለት ችግር ፈቺ የቴክኖሎጂ መተግበሪያዎችን መፍጠራቸውን ገልጸዋል።

በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ባገኙት ዕውቀትና ክህሎት ያበለጸጓቸውን መተግበሪያዎች በቀጣይ የህብረተሰቡን ችግር ለመፍታት እንዲውሉ የፈጠራ ሥራቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም