ቀጥታ፡

በትግራይ ክልል የተቋረጡ የንግድና የማህበራዊ አገልግሎቶች ወደ ስራ ተመልሰዋል


አዲስ አበባ፤ ህዳር 19/2019 (ኢዜአ)፦ በትግራይ ክልል የተቋረጡ የንግድና የማህበራዊ አገልግሎቶች ወደ ስራ መመለሳቸውን የክልሉ ባለአደራ አስተዳደር የኢኮኖሚ እና መልሶ ግንባታ ዋና አስፈጻሚ ቴዎድሮስ አረጋይ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከትግራይ ባለአደራ አስተዳደር ጋር የክትትል ግምገማ ውይይት አድርገዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ ከባለአደራ አስተዳደሩ በተደረገው ውይይት የታዩ ርምጃዎችን፣ ተግዳሮቶችን እና የጋራ የቅድሚያ ጉዳዮችን መገምገማቸውን ገልጸዋል።

የትግራይ ክልል ባለአደራ አስተዳደር የኢኮኖሚ እና መልሶ ግንባታ ዋና አስፈጻሚ ቴዎድሮስ አረጋይ (ዶ/ር) ባለፉት 45 ቀናት ውስጥ የስድስት ወር እቅዱን መነሻ በማድረግ የመጀመሪያ ምዕራፍ የአስተዳደር፣ የሰላምና የመልሶ ማቋቋም ስራዎች በስፋት መከናወናቸውን ገልጸዋል።

በዞኖችና በወረዳዎች አመራሮችን በመመደብ የአስተዳደር ስራዎች እንዲቀጥሉ መደረጉንና የወደሙ ቢሮዎችን በመጠገን የፐብሊክ ሰርቪስ አገልግሎት መጀመሩን አመልክተዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን የሰላምና ጸጥታ ስጋቶችን በሂደት በማስተካከል ህብረተሰቡ በተረጋጋ ሁኔታ እንዲሰራ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ተናግረዋል።

በኢኮኖሚና ማህበራዊ ዘርፍም የንግድ እንቅስቃሴዎች እንዲጀመሩና ነዳጅ ወደ ክልሉ እንዲገባ መደረጉን ነው ያብራሩት።

የትምህርት፣ የጤናና የማህበራዊ ጉዳይ አገልግሎቶች እንዲቀጥሉ መደረጉን አስረድተዋል።

እንዲሁም የወደሙ መሰረተ ልማቶችን ጠግኖ ወደ አገልግሎት የማስገባትና በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች እርዳታ በአግባቡ እንዲደርስ የማድረግ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።

በቀጣይ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው መመለስ፣ የእርዳታ ስራውን ማጠናከር እና ከህዝብ ጋር ያለውን ግንኙነት በማጠናከር የሰላም አካል ማድረግ ቀዳሚ ትኩረት መሆኑን ነው የገለጹት።

እስካሁን ጥገና ያልተደረገላቸውን መንገዶች፣ የመብራትና የኢትዮ ቴሌኮም መሰረተ ልማቶችን ጠግኖ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠትም ከፍተኛ ጥረት እንደሚደረግም ዋና አስፈጻሚው አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም