በሲዳማ ክልል በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር በንብ ማነብ ሥራ የተሰማሩ ዜጎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤታማ እየሆኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሲዳማ ክልል በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር በንብ ማነብ ሥራ የተሰማሩ ዜጎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤታማ እየሆኑ ነው
ሀዋሳ፤ ህዳር 19/2019 (ኢዜአ)፦በሲዳማ ክልል በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር በንብ ማነብ ሥራ የተሰማሩ ዜጎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤታማ በመሆን ገቢያቸውን እያሳደጉ መምጣታቸውን ገለጹ።
የሲዳማ ክልል እንስሳት ሀብት ልማት ቢሮ በበኩሉ በበጀት ዓመቱ ከ7 ሺህ ቶን በላይ የማር ምርት ለመሰብሰብ ግብ ተይዞ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት በተጀመረው የሌማት ትሩፋት መርሀ ግብር ትኩረት ከተሰጣቸው አንዱ የማር ምርትና ጥራትን በማሳደግ ከቤት ውስጥ ፍጆታ ባለፈ ለገበያ በማቅረብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ነው።
በማር ልማት ላይ የተጀመረው ይህ ሀገራዊ ንቅናቄ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር ተጨማሪ የገቢ ምንጭ እየሆነም መጥቷል።
በተለይ የንብ ማነብ ሥራው ከሌሎች የግብርና ሥራዎች ጎን ለጎን የሚካሔድ መሆኑ ብዙዎች በልማቱ በመሳተፍ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።
በሲዳማ ክልል በንብ ማነብ ሥራው በመሳተፍ ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል በወንዶገነት ወረዳ ወሻ ሶያማ ቀበሌ ነዋሪ መኮንን ደሳለኝ (ዶ/ር)፤ የሌማት ትሩፋት ይፋ መደረጉን ተከትሎ በንብ ማነብ ሥራ ተሰማርተው ውጤታማ እየሆኑ መምጣታቸውን ገልጸዋል።
ሥራውን በባህላዊ ቀፎዎች እንደጀመሩ ገልጸው፣ በአሁኑ ወቅት ከ15 በላይ ዘመናዊ ቀፎዎች እንዳሏቸው ተናግረዋል።
ከእርሻ ሥራቸው ጎን ለጎን የጀመሩት የንብ ማነብ ሥራ ውጤታማ እንዳደረጋቸው የተናገሩት ደግሞ በወረዳው ዎተራና ቀጬማ ቀበሌ ግንባር ቀደም አርሶ አደር ተስፋዬ ዋታ ናቸው።
በጠቅላላው ከ45 በሚበልጡ የሽግግር፣ ዘመናዊ እና ጨፈቃ የንብ ቀፎዎች የንብ ማነብ ሥራ እያከናወኑ መሆናቸውን የገለጹት አቶ ተስፋዬ፣ በዓመት አራት ዙር ከሚቆርጡት ማር እስከ 400 ሺህ ብር ገቢ እንደሚያገኙ ተናግረዋል።
ከሌሎች የግብርና ሥራዎች አንጻር ሲታይ ንብ የማነብ ሥራ ብዙ ወጪ ስለማይጠይቅ ተጠቃሚ አድርጎኛል ሲሉም ገልጸዋል።
የሲዳማ ክልል እንስሳት ሀብት ልማት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አደገ አየለ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንዳሉት፣ በክልሉ ያለውን ሀብት ለይቶ በመጠቀም ዜጎች ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሁኔታ ተፈጥሯል።
በዚህም በርካታ ዜጎች በንብ ማነብ ሥራ ተሰማርተው የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከግንዛቤ ፈጠራ ሥራ ባለፈ የድጋፍና ክትትል ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።
ለንብ ማነብ ሥራው ዘመናዊ ቀፎዎችን ከመጠቀም ባለፈ ህብረተሰቡ በአካባቢው ባሉ ግብአቶች ተጠቅሞ ባህላቂ የጨፈቃ ቀፎ በመስራት እንዲጠቀም መደረጉንም የጠቆሙት ሃላፊው፣ በዚህም በተያዘው በጀት ዓመት ብቻ ከ250 ሺህ በላይ የጨፈቃ ቀፎ ጥቅም ላይ ለማዋል እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በበጀት ዓመቱ ከ7 ሺህ ቶን በላይ የማር ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑንም አደገ (ዶ/ር) አመልክተዋል ።