ቀጥታ፡

ኢንስቲትዩቱ በምርምር ያፈለቃቸውን ምርጥ የሰብል ዝርያዎች ለተጠቃሚዎች ተደራሽ እያደረገ ነው

ሮቤ፤ ህዳር 19/2019 (ኢዜአ)፦የኦሮሚያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በምርምር ያፈለቃቸውን የሰብል ዝርያዎች በራሱ የምርምር ጣቢያዎችና በአርሶ አደሩ ማሳ ላይ በማባዛት ለተጠቃሚዎችና ለባለድርሻ አካላት እያቀረበ መሆኑን ገለጸ።

የሲናና ግብርና ምርምር ማዕከል የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎችን ለተጠቃሚዎች ተደራሽ የማድረግ ተግባራትን የሚገመግም የመስክ ምልከታ ተካሂዷል።

በዚህ ወቅት የኦሮሚያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ተወካይ ደረጄ ወልተጂ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ኢንስቲትዩቱ በምርምር የተገኙ ዝርያዎችን በራሱና በአርሶ አደሩ ማሳ ላይ በማባዛት ለተጠቃሚው ተደራሽ እያደረገ ነው።


 

ኢንስቲትዩቱ አዳዲስ ዝርያዎችን፣ የአሠራር ዘዴዎችንና ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶ አደሩ ተደራሽ በማድረግ ዘርፉን ለማዘመን እየሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

በተለይም በኢንስቲትዩቱ ሥር የተደራጁ 17 የግብርና ምርምር ማዕከላት ባለፈው ዓመት ብቻ በሰብል ልማት፣ በጥራጥሬ፣ በእንስሳት መኖና በሌሎችም 34 የተለያዩ የምርምር ውጤቶችን ለተጠቃሚው ተደራሽ ማድረጋቸውን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

የሲናና ምርምር ማዕከል በራሱ ማሳና በበኩታ ገጠም አሠራር ተደራጅተው በሚሠሩ አርሶ አደሮች ማሳ ላይ እያካሄደ ያለው የዘር ብዜትና የምርምር ሥራዎች የዚሁ ጥረት ማሳያና እንደ ተሞክሮ የሚወሰዱ ናቸው ሲሉም አክለዋል።

እንደ ደረጄ (ዶ/ር) ገለጻ፣ ኢንስቲትዩቱ እያከናወናቸው ያሉ የምርምር ሥራዎች በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገውን ሀገራዊ ጥረት ጨምሮ ለግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ግቦች ስኬታማነት የራሳቸውን አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ናቸው።


 

የሲናና ግብርና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው አሰፋ በበኩላቸው፣ ማዕከሉ የተለያዩ የተሻሻሉ የሰብልና ሌሎች ዝርያዎችን በምርምር በማፍለቅና ከአጋዥ አካላት ጋር በትብብር በማባዛት ለአርሶ አደሩ እያቀረበ ይገኛል።

ማዕከሉ ባለፈው ዓመት ብቻ 12 የተለያዩ የተሻሻሉ ዝርያዎችን በምርምር በማውጣት ለተጠቃሚው ማድረሱንም በማሳያነት ጠቅሰዋል።

በአሁኑ ወቅትም ማዕከሉ የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎችን፣ የእንስሳት መኖን እና ሌሎች አዳዲስ የዘር ብዜቶችን ለአርሶ አደሩና ለአርብቶ አደሩ ተደራሽ ለማድረግ ከ200 ሄክታር በሚበልጥ የራሱና የአርሶ አደሩ ማሳ ላይ እያባዛ መሆኑን ተናግረዋል።

ማዕከሉ በየጊዜው የሚለቀቁ አዳዲስ ዝርያዎችን ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በስፋት በማባዛት አርሶ አደሩ እንዲጠቀምባቸው የማድረጉን ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አቶ ጌታቸው አስታውቀዋል።


 

ከአጋርፋ ወረዳ አሊ ቀበሌ አርሶ አደሮች መካከል አቶ አህመድ ጠይብ በሰጡት አስተያየት እንዳሉት፣ ቀደም ሲል የተሻሻለ ዘር በማይጠቀሙበት ወቅት ከአንድ ሄክታር የሚያገኙት የስንዴ ምርት ከ20 ኩንታል አይበልጥም ነበር።

ከአራት ዓመታት ወዲህ ከምርምር ማዕከሉ ያገኙትን የስንዴ ዝርያ ተጠቅመው በማምረት ከአንድ ሄክታር 65 ኩንታል ምርት ማግኘት እንደቻሉ ገልጸዋል።

"የምርምር ማዕከሉ የተሻሻሉ ዝርያዎችን በቅርበት እንድናገኝ ከማድረጉ ባሻገር ምርታማነትን ከሚያሳድጉ የግብርና አሠራሮች ጋር እንድንተዋወቅ ረድቶናል" ያሉት ደግሞ ሌላው የወረዳው አርሶ አደር አቶ እሸቱ ከተማ ናቸው።


 

በ1978 ዓ.ም የተቋቋመው የሲናና ግብርና ምርምር ማዕከል እስካሁን ድረስ በሰብል ዝርያ፣ በእንስሳት መኖ፣ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ፣ በቡናና ሌሎች የትኩረት መስኮች ከ128 በላይ የምርምር ውጤቶችን ለተጠቃሚው ማድረሱ ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም