በትግራይ ክልል የአስተዳደር መዋቅር ምስረታ፣ የሰብዓዊ ድጋፍና የምርጫ ዝግጅት ስራዎች አበረታች ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
በትግራይ ክልል የአስተዳደር መዋቅር ምስረታ፣ የሰብዓዊ ድጋፍና የምርጫ ዝግጅት ስራዎች አበረታች ናቸው
አዲስ አበባ፤ ህዳር 19/2019 (ኢዜአ)፦ በትግራይ ክልል የአስተዳደር መዋቅር ምስረታ፣ የሰብዓዊ ድጋፍና የምርጫ ዝግጅት ሂደት በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የክልሉ ባለአደራ አስተዳደር የአስተዳደርና የሕዝብ አገልግሎት ዋና አስፈጻሚ አቶ አሰፋ አብርሃ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከትግራይ ባለአደራ አስተዳደር ጋር የክትትል ግምገማ ውይይት አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ ከባለአደራ አስተዳደሩ ጋር በተደረገው ውይይት የታዩ ርምጃዎችን፣ ተግዳሮቶችን እና የጋራ የቅድሚያ ጉዳዮችን መገምገማቸውን ገልጸዋል።
የትግራይ ክልል ባለአደራ አስተዳደር የአስተዳደርና የሕዝብ አገልግሎት ዋና አስፈጻሚ አቶ አሰፋ አብርሃ ፤ አስተዳደሩ የክልል መንግስት መዋቅርን እንደገና በማደራጀት የማቋቋም ስራ ማከናወኑን አመልክተዋል።
በዚህ ጊዜ ውስጥ በቀበሌና ከወረዳ ምርጫ በማድረግ አዲስ አመራርና መዋቅር መዘርጋቱን፣ የዞን አመራር መቋቋሙን እንዲሁም የተሟላ የክልሉ ካቢኔ ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱን ገልጸዋል።
ከዚህ ጎን ለጎን የፍትህ፣ የዳኞች፣ የፖሊስና የሚሊሻ አደረጃጀቶች መጠናከራቸውን እና ከተሞችን ከወንጀል በማጽዳት በብዙ ከተሞች ጸጥታና ፍትህ ማስፈን የሚችል አስተዳደር መመስረቱን ተናግረዋል።
ባለፉት ቀናት ብቁና ኃላፊነት የሚሰማው የሰው ኃይል የመምረጥና የመመደብ ስራ መከናወኑን የጠቆሙት ዋና አስፈጻሚው፣ ቀጣዩ ዋነኛ ስራ የተመደቡ አመራሮችንና የተቀመጠውን በጀት በተግባር በመፈተን፣ በመከታተልና በመገምገም አቅምን ማጠናከር መሆኑን ነው የገለጹት።
በሌላ በኩል በተለይ በደቡብ ትግራይ፣ በምስራቅና በተምቤን አካባቢዎች የሚገኙ ዜጎችን ለመደገፍ የተከማቸ እርዳታና እህልን በማውጣት እንዲሁም ከሀገር ውስጥና ከውጭ የሚሰበሰቡ ድጋፎችን በመጠቀም የሰውን ህይወት የማትረፍና የመደገፍ ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
ቀጣዩ ዋነኛ ትኩረት በስድስት ወራት ውስጥ የተሳካ ምርጫ በማካሄድ ስልጣንን በሰላም በህዝብ ወደተመረጠ መንግስት ማሸጋገር መሆኑን ገልጸው፣ በመቀሌ የምርጫ ቦርድ እንቅስቃሴ መጀመሩን ጠቁመዋል።
ተፈናቃዮችን ወደ ቀዬያቸው የመመለስ ተግባርም በቀጣይ ዙር በቅድሚያ የሚሰራበት እንዲሆን አቅጣጫ መቀመጡን አክለዋል።
በአጠቃላይ በእነዚህ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሰራ በተሰጠው መመሪያ መሰረት በተገኘው ውጤት አመራሮች መደሰታቸውን አቶ አሰፋ ገልጸዋል።
በዛሬው ውይይታቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለቀጣይ ስራዎች ሙሉ ድጋፍ እንደሚያደርጉ በማረጋገጥ አመራሮቹን ማበረታታቸውንም አስታውቀዋል።