ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ከራሷ አልፎ የቀጣናውን የሃይል ሚዛን ለማስጠበቅ ወሳኝ ሚና አለው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 19/2019 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ከራሷ አልፎ የቀጣናውን የሃይል ሚዛን ለማስጠበቅ ወሳኝ ሚና እንዳለው በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የመካከለኛው ምሥራቅና የእስያ ፓስፊክ ጉዳዮች ከፍተኛ ተመራማሪ አንተነህ ጌታቸው (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ ለቀይ ባሕር አካባቢ ሀገራት “በሰጥቶ መቀበል መርህ አብረን እንልማ” ሲሉ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወቃል።

የቀይ ባሕር ጉዳይ የመሬት ብቻ ሳይሆን የአየር ጭምር መሆኑን ገልጸው፤ ኢትዮጵያ በምድርም በሰማይም ተዘግቶባት ሰላም የሚሰፍንበት ቀጣና እና አህጉር እንደማይኖር ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በትብብርና ወንድማማችነት መንፈስ ለመልማት ፅኑ አቋምና ቁርጠኝነት እንዳላትም አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በጋራ ለማደግ ያቀረበቻቸውን ሐሳቦች በማንሳት፣ በትብብርና በወንድማማችነት መንፈስ ከቀጣናው ሀገራት ጋር በጋራ ለመልማት ያላትን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።

በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የመካከለኛው ምሥራቅና የእስያ ፓስፊክ ጉዳዮች ከፍተኛ ተመራማሪ አንተነህ ጌታቸው (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት የህልውና ጉዳይ መሆኑ ሁሉም የሚስማማበት ነው።

ኢትዮጵያ ካላት መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ፣ የምታስመዘግበው ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገትና የህዝብ ብዛት አንጻር የባህር በር የግድ ያስፈልጋታል ብለዋል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የኢትዮጵያን የንግድና ኢንቨስትመንት ተመራጭ መዳረሻነት አሳድጓል ያሉት ተመራማሪው፤ የቀጣናው ተለዋዋጭነትና በአካባቢው ያላትን ተጽዕኖ ፈጣሪነት ለማስቀጠል የባህር በር እንደሚያስፈልጋት ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ከራሷ አልፎ በአፍሪካና ዓለም አቀፍ ደረጃ በሰላም ማስከበር ተልዕኮ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳላት ገልጸው፤ ከታሪክ፣ ከዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትና ባህል አንፃር ከባህር በር ዝግ መሆን አይገባትም ብለዋል።

የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ከራሷ አልፎ ቀጣናዊ የሃይል ሚዛኑን ጠብቆ ለማቆየት ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም