ቀጥታ፡

የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር ከአካባቢ ጥበቃ ባለፈ በፍራፍሬ ልማት ተጠቃሚ አድርጎናል - አርሶ አደሮች

ሀዋሳ፤ ህዳር 19/2019 (ኢዜአ)፦የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር ከአካባቢ ጥበቃ ባለፈ በፍራፍሬ ልማት በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው በሲዳማ ክልል የዳሌ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ።

በሲዳማ ክልል ዳሌ ወረዳ በአቮካዶ ምርት የተሰማሩ አርሶ አደሮች ‎የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር የአካባቢያቸውን ሥነምህዳር ከማስተካከል ባለፈ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን እንዳሳደገላቸው ለኢዜአ ገልፀዋል፡፡

ከወረዳው አርሶ አደሮች መካከል አቶ ተገኝ ጉጆ በ1 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ላይ የተሻሻለ ዝርያ ያላቸውን የአቮካዶ ተክሎች እያለሙ መሆናቸውን ገልጸዋል።


 

ከዚህ በፊት በጓሯቸው አቮካዶ በዘልማዳዊ መንገድ ተክለው ሲያለሙ ብዙም ተጠቃሚ እንዳልነበሩ አስታውሰው፣ የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብርን ተከትሎ የተሻሻሉ የአቮካዶ ዝርያዎችን በተደራጀ መንገድ በብዛት እያለሙ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ይህም የተፈጥሮን ሥነ ምህዳር እየጠበቁ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።፡


 

በአሁን ወቅት በዓመት 110 ኩንታል ጥራት ያለው የአቮካዶ ምርት አባል በሆኑበት የአምራች ማህበራቸው በኩል ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚነታቸውን እያሳደጉ መምጣታቸውን አመልክተዋል።

አርሶ አደር አያንቱ ገርማሞ በበኩላቸው ከግማሽ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ ከሚያለሙት የአቮካዶ ተክል በዓመት እስከ 50 ኩንታል ምርት በመሰብሰብ ለገበያ እንደሚያቀርቡ ገልፀዋል፡፡


 

ዝርያቸው የተሻሻለ የአቮካዶ ተክሎችን በስፋት በመትከልና በማህበር በመደራጀት ምርታቸውን ለግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክ በማቅረብ የተሻለ የኢኮኖሚ ጥቅም እያገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የዳሌ ወረዳ ቡና፣ ፍራፍሬና ቅመማ ቅመም ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዓባይነህ ዌና በወረዳው በየዓመቱ የተሻሻለ ዝርያ ያላቸውን የአቮካዶ ችግኞች በመንግሥት፣ በማህበራትና በአርሶ አደሮች ደረጃ በስፋት በማፍላት ለአርሶ አደሩ የማከፋፈል ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡


 

ምርቱን ለይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ በተደራጀ መንገድ ለማቅረብ የተቋቋሙ ማህበራት በሥራቸው ያሉ አርሶ አደሮች የገበያ ችግር እንዳይገጥማቸው ጉልህ አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

የሲዳማ ክልል ቡና፣ ፍራፍሬና ቅመማ ቅመም ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ታሪኩ ዶንቃ በበኩላቸው፣ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር በክልሉ የፍራፍሬ ልማት በማሳ ሽፋንና በምርት መጠን እንዲድግ የላቀ ሚና መጫወቱን አንስተዋል።


 

ለአብነት በ2016 ዓ.ም 359 ሺህ 113 ቶን የነበረው የፍራፍሬ ምርት በሁለት ዓመት ውስጥ ብቻ እመርታ በማሳየት ባለፈው ዓመት 582 ሺህ 874 ቶን መድረሱ ምርትና ምርታማነት በእጅጉ እያደገ መምጣቱን ያሳያል ብለዋል።

በተለይ በአቮካዶ ምርት ሰንሰለት ላይ በችግኝ ማፍላት፣ በማምረት፣ በግብይትና በሌሎች ሥራዎች የተሰማሩ በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች የኢኮኖሚ ተጠቃሚ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብርም ከ7ሺህ 400 ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የፍራፍሬ ችግኞችን ለመትከል ከወዲሁ የችግኝ ዝግጅት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም