ቀጥታ፡

በደቡብ ምዕራብ ኦሮሚያ ዞን ባለፉት አራት ወራት 13 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ገቢ ተሰብስቧል

ጅማ፤ ህዳር 19/2019 (ኢዜአ)፦በደቡብ ምዕራብ ኦሮሚያ ዞን ባለፉት አራት ወራት 13 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን የዞኑ ገቢዎች ጽሕፈት ቤት ገለጸ።

አዲሱ የዞን አደረጃጀት ለገቢ አሰባሰቡ መጠናከር ጉልህ አስተዋጽኦ ማድረጉ ተመላክቷል።

የደቡብ ምዕራብ ኦሮሚያ ዞን ገቢዎች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ካሳሁን ታደለ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በዞኑ በበጀት አመቱ 37 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ ተግባራዊ እየተደረገ ነው።

ባለፉት አራት ወራት በተደረገ እንቅስቃሴ 13 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን ተናግረዋል።

የተሰበሰበው ገቢ ከአጠቃላይ እቅዱ 36 ነጥብ 2 በመቶ ድርሻ እንዳለው ጠቁመው የበጀት አመቱን እቅድ ለማሳካት ከወዲሁ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ገቢው ቀጥተኛና ቀጥተኛ ካልሆኑ ታክሶች እንዲሁም ከማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች የተሰበሰበ መሆኑንም ተናግረዋል። 

በክልሉ በአዲሱ የዞን አደረጃጀት  የተፈጠረው የአሠራርና የቁጥጥር ምቹ ሁኔታ የገቢ አሰባሰብን እያሳለጠና እያጠናከረ መሆኑንም አመልክተዋል ።

አደረጃጀቱ በተለይም  ሕገወጥ ንግድን ከመከላከልና የገቢ አሰባሰብ ሥራን ከማቀላጠፍ አኳያ ጉልህ ሚና እየተጫወተ መሆኑን አብራርተዋል።

አዲሱን አደረጃጀት ተከትሎ በተፈጠረው የተሻለ የቁጥጥር ሥርዓት 1 ሺህ 600 ሕገወጥ ነጋዴዎችን የመለየት ሥራ መከናወኑንና ወደ ሕጋዊ ሥርዓት የማስገባት ሥራም እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።


 

የዞኑን የገቢ አሰባሰብና ክትትል ሥራን ለማቀላጠፍ በአራት ክላስተሮች ተከፋፍሎ እየተመራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የዞኑ ገቢዎች ጽሕፈት ቤት የገቢ ክትትል ባለሙያ አቶ ሰዴታ ደረጀ ናቸዉ።

እንደ ባለሙያው ገለጻ፣ የገቢ አሰባሰብና ክትትል ሥራውን ለማሳለጥ ዞኑ በኢሉ አባቦር፣ በሊሙ፣ በጅማና በቡኖ በደሌ በአራት ክላስተሮች ተደራጅቶ እየሠራ ሲሆን፣ አሠራሩም ውጤታማ እየሆነ ነው።


 

የደቡብ ምዕራብ ኦሮሚያ ዞን መንቾ ወረዳ ነዋሪ አቶ ሚስባሁ ጂሀድ በበኩላቸው፣ በጽሕፈት ቤቱ የሚሰጠው አገልግሎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም ቀናትን የሚፈጁ አገልግሎቶችን አሁን በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ማግኘት እየቻሉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም