"የዓባይ ዘመን ብዕር" ስለ ዓባይ የተነገሩ ሃዘን፣ መፋዘዝና እንጉርጉሮን በተስፋ ተክቷል - የሥነ-ፅሁፍ ባለሙያዎች - ኢዜአ አማርኛ
"የዓባይ ዘመን ብዕር" ስለ ዓባይ የተነገሩ ሃዘን፣ መፋዘዝና እንጉርጉሮን በተስፋ ተክቷል - የሥነ-ፅሁፍ ባለሙያዎች
አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 26/ 2012 ( ኢዜአ) "የዓባይ ዘመን ብዕር" ስለ ዓባይ የተነገሩ እንጉርጉሮ፣ ሃዘንና መፋዘዝን በተስፋ፣ በመጪው ጊዜ ትንበያና ጥልቅ ምርምር በሚሹ ስራዎች የተካ የግጥም መድበል።
የኢትዮጵያ ፀጋ የሆነው 'ዓባይ' ዝንተ ዓለም መፍሰሱ ያስቆጫቸው ባለቅኔና ደራሲያን፤ ገጣሚያንና የጥበብ ሰዎች ቁጭት አዘል ስራዎቻቸውን በሙዚቃ፣ በሥነ-ፅሑፍ፣ በስዕል ወደ ቤቱ የሚመለስበትን ዘመን ሲናፍቁ ኖረዋል።
የዓባይን የስልጣኔ፣ የሃብት፣ የኩራት፣ የውበት ምንጭነትና የአገር ቅርስነት በቁጭት ሲያወሱት ኖረዋል፤ ዓባይ ተሞግሷል፣ ዓባይ እንደ ሰው ተወቅሷል፣ ዓባይ ተሰድቧል።
ይሁንና የዓባይን ታሪክ የቀየረውና ኢትዮጵያዊያን በአንድ ዓይን እንዲመለከቱ ያደረገው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ጥበበኞቹንም ተስፋን የሰነቁ ስራዎች ይዘው እንዲወጡ ዕድል ሰጥቷቸዋል።
በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ፅህፈት ቤት የተዘጋጀውና 50 አንጋፋና ወጣት ደራሲያን የተሳተፉበት "የዓባይ ዘመን ብዕር" የግጥም መፅሃፍ ተጠቃሽ ነው።
መጽሐፉ ዓባይን የተመለከቱ ወጥ ሥነ-ግጥሞች፣ ወግና የዘፈን ግጥሞች ተካተውበታል፤ ብዙዎች ቁጭታቸውን በብሩህ ተስፋ በማለምለም የድርሻቸውን እንዲወጡም ያሳስባል።
የመጽሐፉ ቅጂዎች ለታሪክ፤ ለምርምርና ለማጣቀሻነት እንዲውሉ ሆነው የተዘጋጁም ናቸው።
በዚህ መጽሐፍ 10 ግጥሞቹን አካቶና የአጋሮቹንም ሰንዶ ያዘጋጀው ደራሲና ገጣሚ አንዱዓለም አባተ /የአፀደ ልጅ/ አብዛኞቹ ዓባይን የተመለከቱ ግጥሞች እንጉርጉሮ፣ ሀዘንና መፋዘዝ ላይ ያተኮሩ ስለመሆናቸው ያነሳል።
"የዓባይ ዘመን ብዕር" ግን ተስፋን የሰነቁ፣ ቀጣዩን ጊዜ የተነበዩና ጥልቅ ምርምርን የሚጠይቁ ሥራዎች እንደተካተቱበት ነው የገለፀው።
መጽሐፉ አዲሱ ትውልድ ገጣሚዎቹና ማኅበረሰቡ ስለ ዓባይ ምን ያሳስባቸው እንደነበረ የሚረዳበት፤ ስለ ዓባይ ቀድመው ለፃፉ እውቅና የሚሰጥበት እንደሆነም ነው የተናገረው።
በየቤታቸው ሆነው ስለ ዓባይ የገጠሙም ይነቃቁበታል ይላል ደራሲና ገጣሚ አንዱዓለም አባተ።
እንደ ደራሲው ገለፃ በመጽሐፉ ስለ ዓባይ ከተባሉት የተመረጡ ግጥሞች ታተሙ እንጂ ኢትዮጵያዊያን ለዘመናት ስለ ዓባይ ሲገጥሙ ኖረዋል።
ደራሲና ሃያሲ አያልነህ ሙላት "የዓባይ ዘመን ብዕር" ግጥሞች በስዕላዊ መግለጫ ዳብረው ለማስተማሪያነት ጭምር በስፋት ሊሰራጩ ይገባል ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።
የመጽሐፉን ስርጭት ከፍ ማድረግ እንደሚያስፈልግና የዓባይን ጉዳይ ለዓለም ሕዝብ ለማስረፅም በተለያዩ ቋንቋዎች መተርጎም አለበት ሲልም ሃሳብ ሰንዝሯል።
በተለይም ወደ ዓረብኛና እንግሊዝኛ ቢተረጎሙ ግብፆች እውነቱን እንዲረዱና በእጅ አዙርም የዓባይን ጉዳይ ሊቆለምሙ ለሚሞክሩት ምዕራባዊያን ግንዛቤ ለመስጠት ይረዳል ብሏል ሃያሲው።
ለመጀመሪያ ጊዜ የታተመው "የዓባይ ዘመን ብዕር" መፅሐፍ ሶስት ምዕራፎችና 237 ገፆች አሉት።