በቤይሩት የነበሩ 90 ኢትዮጵያዊያን ወደ አገራቸው ተመለሱ - ኢዜአ አማርኛ
በቤይሩት የነበሩ 90 ኢትዮጵያዊያን ወደ አገራቸው ተመለሱ
አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 26/ 2012 ( ኢዜአ) በቤይሩት ይኖሩ የነበሩ 90 ኢትዮጵያዊያን ዛሬ ወደ አገራቸው መመለሱን በቤይሩት የኢትዮጵያ ቆንስላ ጄኔራል ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
ቆንስላ ጄኔራል ጽህፈት ቤቱ በሊባኖስ ሁለት እስር ቤቶች ታስረው የነበሩ 19 ዜጎችን ከፍርድ ቤቶችና እስር ቤቶቹ ጋር በመነጋገርና በማስፈታት የጉዞ ሰነዶቻቸው እስኪጠናቀቁላቸው በኢትዮጵያ ኮሙኒቲ ማህበር መጠለያ እንዲቆዩ መደረጉን ገልጿል።
ከእነዚህ ዜጎች መካከል 18ቱ የኮቪድ-19 ምርመራ ተደርጎላቸው ነጻ መሆናቸው ተረጋግጦ የጉዞ ሰነዳቸውና የመውጫ ቪዛ ተሰርቶላቸው ዛሬ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል።
የትራንስፖርት ወጪያቸውን በራሳቸው በመሸፈን በ8ኛው ዙር ወደ አገራቸው ለመመለስ ተመዝግበው ሲጠባበቁ የነበሩ 71 ዜጎችና ሆስፒታል ውስጥ የነበረች አንዲት ሴትም ዛሬ ከገቡት መካከል ናቸው።
በተመሳሳይ ዛሬ ምሽትን ጨምሮ በቀጣዮቹ ቀናት 155 ኢትዮጵያዊያን ወደ አገራቸው እንደሚመለሱ ቆንስላ ጄኔራል ጽህፈት ቤቱ በማኅበራዊ ድረ ገጹ አስፍሯል።