ድርጅቱ ኮሮናን ለመከላከል ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ድርጅቱ ኮሮናን ለመከላከል ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ
መተማ ነሐሴ 26/2012 (ኢዜአ) የአለም ፍልሰተኞች ድርጅት (አይ ኦ ኤም) በምዕራብ ጎንደር ዞን የኮሮናቫይረስ መከላከል ስራን ለማገዝ አንድ ሚሊዮን 500 ሺህ ብር ግምት ያለው ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።
ድርጅቱ ያደረገው ድጋፍ በዞኑ ኮሮናን ለመከላከል በተቋቋሙ የለይቶ ማቆያዎች የቁሳቁስ እጥረት እንደሚያቃልል ተመልክቷል ።
የዞኑ የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል የሀብት አሰባሳቢ ኮሚቴ ሰብሳቢና የዞኑ አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ምቹ ወረቀት በርክክብ ስነ ስርዓቱ ላይ እንደገለጹት ዞኑ ከሱዳን ጋር የሚዋሰን በመሆኑ ለኮሮና ቫይረስ ስርጭት ከፍተኛ ተጋላጭ ነው።
በዞኑ የቫይረሱ ስርጭት የተጋላጭነት ስጋት በመገንዘብ በርካታ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የአለም ፍልሰተኞች ድርጅትም የአሁኑን ድጋፍ ሲያደርግ ለሶስተኛ ጊዜ መሆኑን የገለጹት አቶ ምቹ ድጋፉ ኮሮናን ለመከላከል በተቋቋሙ አስገዳጅ ለይቶ ማቆያዎች የቁሳቁስ እጥረት እንደሚያቃልል አመላክተዋል ።
ድርጅቱ ድጋፍ ካደረጋቸው ቁሳቁሶች መካከል ብርድ ልብሶች፣ ድንኳኖች፣ የንጽህና መጠበቂያ ሳሙናዎች፣ የምግብ ማብሰያዎችና ሳኒታይዘር እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።
ድርጅቱ ከቁሳቁስ ድጋፍ በተጨማሪ በማቆያ ቦታዎች ድጋፍ የሚሰጡና መረጃ የሚሰበስቡ ባለሙያዎችን በኮንትራት በመቅጠር ቫይረሱን የመከላከል ስራን እያገዘ ነው" ያሉት ደግሞ የግብረኃይሉ አባል አቶ ዮናስ ጋዲሳ ናቸው፡፡
ድርጅቱ በተጨማሪም ሱዳን በቀን ስራ ቆይተው ወደ ሀገር ለሚመለሱና ወደ መኖሪያ አካባቢያቸው ለሚሄዱ ሰዎች የትራንስፖርት ወጪን ለመሸፈን ቃል መግባቱንም ተናግረዋል።
በዞኑ እየተካሄደ ላለው የኮሮና መከላከል ስራ እስካሁን 10 ሚሊዮን 400 ሺህ ብር ጥሬ ገንዘብና 9 ሚሊዮን 500 ሺህ ብር ግምት ያለው ቁሳቁስ ተሰብስቦ ጥቅም ላይ መዋሉን የግብረሀይሉ መረጃ አመላክቷል ።