ቀጥታ፡

በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መረሃ ግብር ለ314 ሺህ ዜጎች የስራ እድል ተፈጥሮላቸዋል

አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 26/ 2012 ( ኢዜአ) በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መረሃ ግብር ለ314 ሺህ ዜጎች የስራ እድል መፍጠሩን የአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን አስታወቀ።
የኮሚሽኑ ኮሚሸነር ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ ለኢዜአ እንደገለጹት የአረንጓዴ ልማት የአየር ንብረት ለውጥ መዛባትን ከመከላከል በተጨማሪ በሂደቱ ለበርካቶች የስራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል።

በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መረሃ ግብር ከ314 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል ያስገኘላቸው መሆኑንም ተናግረዋል።

በሌላ በኩል የተተከሉ ችግኞችን በመንከባከብ ሂደት ወጣቶች የስራ እዲል እያገኙ መሆኑንም ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።

በተለያዩ ተቋማትም ይሁን ግለሰቦች የሚተከሉ ችግኞችን ለመንከባከብ ወጣቶች ስምምነት በመፍጠር እየተከፈላቸው በመንከባከብ ላይ ይገኛሉ።

በተፈጠረላቸው የስራ እድል ተጠቃሚ በመሆናቸው መደሰታቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው ወጣቶች ተናግረዋል።

አሁን የተፈጠረው የስራ እድል የሚያበረታታ ቢሆንም በቀጣይ ደግሞ ምቹ የችግኝ ማፍያ ስፍራዎችን መንግስት እንዲያመቻችላቸውም ወጣቶቹ ጠይቀዋል።

ፕሮፌሰር ፍቃዱ እንደሚሉት የአረንጓደ ልማት መርሃ ግብሩ ለወጣቶች የስራ እድል ከመፍጠር ባለፍ ለተፈጥሮ ሃብት እንክብካቤ የሚኖራቸውን አመለካከል የሚያስተካክል ነው።

ወጣቶች ጊዜያቸውን በአልባሌ ቦታ እንዳያሳልፉና ሰርቶ መለወጥን እንዲያስቡም መንገድ የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።

የዘርፉን ልማት ለማጠናከርና የወጣቶችን ተሳትፎ ለማጎልበት በቀጣይ ትኩረት የሚደረግበት መሆኑን ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ሚዛን  እና ስነ ምህዳር  ለመጠበቅ  በአረንጓደ ልማት መርሃ ግብር የሁሉም ተሳትፎ ይጠበቃል።

በዘንድሮው የክረምት ወቅት የተሳካው የ5 ቢሊዮን ችግኞች ተከላም በሚቀጥለው አመት በ6 ቢሊዮን ለማሳካት ከወዲሁ መታቀዱን ፕሮፌሰር ፍቃዱ ገልጸዋል።

ችግኞችን መትከል ብቻውን ስኬት ባለመሆኑ በመንከባከብና በማፅደቅም የህዝቡ ተሳትፎ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም