ቀጥታ፡

የጌዴኦ ወጣቶች ህብረተሰቡን ከኮሮና ቫይረስ ለመጠበቅ ድጋፍ እያደረጉ ነው

ዲላ ነሐሴ 26/2012 (ኢዜአ) በጌዴኦ ዞን በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ የተሰማሩ ወጣቶች ህብረተሰቡን ከኮሮና ቫይረስ ለመጠበቅ ድጋፍ እያደረጉ ነው።

የዲላ ከተማ ነዋሪዋ ወጣት ብሩክታይት በቀለ  እንደገለጸችው በበጎ ፈቃድ ከተሰማሩ የዞኑ ወጣቶች ጋር በመሆን ጭንብል ገዝተው መጠቀም ለማይችሉ ወገኖች ድጋፍ ለማድረግ በማሰብ "ማስክ ፎር ጌዴኦ" በሚል በማህበራዊ ሚዲያ ቅስቀሳ እያደረጉ ነው።

እስካሁን ባካሄዱት እንቅስቃሴ ከ85 ሺህ ብር በላይ በማሰባሰብ እየታጠበ ለአገልግሎት የሚውሉ ከ4 ሺህ በላይ ጭንብል  ከኢንዱስትሪያል ፓርክ በመግዛት ማሰራጨታቸውን  ገልጻለች።

ጭምብሉ ያሰራጩት በዞኑ ሁሉም ወረዳዎች በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች መሆኑን  ተናግራለች።

በዚህ ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል የቀን ሰራተኞች፣ ጉልት ቸርቻሪዎች፣ አቅመ ደካማ አረጋዊያንና ጎዳና ተዳዳሪዎች ይገኙበታል።

በጎ ፍቃደኝነት ወሰን  ተሻጋሪ ነው ያለችው ወጣቷ  በቀጣይም ዘመቻውን ወደ ሌሎች አካባቢዎች ለማስፋት እንደሚፈልጉ ገልጻለች።

ማህበራዊ ሚዲያን ለመልካም ተግባር በመጠቀም በአንድ ሳምንት ውስጥ ድጋፉን ማሰባሰባቸውን የተናገረችው  ደግሞ የጨለለቅቱ ከተማ ነዋሪ ወጣት ነፃነት ጌታቸው ናት።

ወጣቶች ማህበራዊ ሚዲያን ለጥላቻና ለትችት ከመጠቀም በመላቀቅ ለበጎ ተግባር ላይ በማዋል ማህበረሰቡን ሊያገለግል ይገባል ብላለች።

ወጣት ቢንያም ሽፈራው በበኩሉ በዞኑ ወረርሽኙን ለመግታት በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ ጭንብል በማሰባሰብ በመሳተፉ ደስተኛ መሆኑን ተናግሯል።

የጭንብል  ስርጭቱም ቤት ለቤትና በጎዳናዎች ላይ መካሄዱን ጠቅሶ  በተጓዳኝም  በኮሮና መከላከል ዙሪያ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ እያከናወኑ እንደሚገኙ ገልጿል።

ህብረተሰቡን ከኮሮና ቫይረስ ለመጠበቅ  የሚሰጡት ድጋፍ አሁንም ቀጥለው እንዳሉ ወጣቶቹ አመልክተዋል።

የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል አባልና የጌዴኦ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ፍቅሩ በደቻ በበኩላቸው ወጣቶች ያደረጉት ዘመቻ በዞኑ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የሚደረገውን ጥረት አጋዥ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይ በከተሞች በቫይረሱ የሚጠቁ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ ችግሩን ለማቃለል የአፍና አፍንጫ ጭንብል እንደሚያግዝ አመልክተዋል።

የጌዴኦ ዞን ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች መምሪያ የወጣቶች ዘርፍ ኃላፊ አቶ አለሙ ፈይሳ እንዳሉት በዞኑ ከ45 ሺህ በላይ ወጣቶች በክረምቱ ለህብረተሰቡ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ።

ወጣቶቹ እየሰጡ ካሉት አገልግሎት መካከል ለህብረተሰቡ የኮሮና ወረርሽን ስለመከላከል ትምህርት መስጠት፤ የአረጋዊያንን ቤት ማደስ፣ ደም ልገሳ ፣ችግኝ መትከልና መንከባከብ ይገኙበታል።

በዞኑ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ እስከ መጪው መስከርም ወር የመጀመሪያዎቹ ሳምንታት ድረስ እንደሚቀጥልም ኃላፊው ገልጸዋል።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም