የአሶሳ አስፓልት መንገድ ብልሽት የከተማውን እድገት እያጓተተው ነው - ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የአሶሳ አስፓልት መንገድ ብልሽት የከተማውን እድገት እያጓተተው ነው - ነዋሪዎች
አሶሳ፣ ነሐሴ 26 / 2012 ዓ.ም(ኢዜአ) የአሶሳ ከተማ አስፓልት መንገድ በጥገና እጦት ለከፋ ብልሽት በመዳረጉ ለእንቅስቃሴ አዳጋች ከመሆኑ ባለፈ የከተማውን እድገት እያጓተተው መሆኑን ነዋሪዎች ገለጹ፡፡
አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ ነዋሪዎች መካከል አቶ ታምራት አባተ እንዳሉት የከተማው አስፓልት መንገድ ረጅም ዓመት ያስቆጠረ ነው፡፡
መንገዱ ወቅቱንና ደረጃውን የጠበቀ ጥገና ስለማይደረግለት ለከፋ ብልሽት መዳረጉን ተናግረዋል ።
መንገዱ የደረሰበት ብልሽት ለእግረኛም ሆነ ለተሽከርካሪ እንቅስቃሴ አስቸጋሪ ከመሆኑ ባለፈ የከተማውን እድገት እያጓተተው መሆኑን አመላክተዋል ።
የነዋሪዎች ቆሻሻ አወጋገድም ፍሳሽ መውረጃዎችን በመድፈን ለመንገዱ ብልሽት አስተዋጽኦ እንዳደረገ ጠቅሰዋል፡፡
የባለሶስት እግር ታክሲ አሽከርካሪ ወጣት በፍቃዱ መሳይ በበኩሉ መንገዱ ለተሽከርካሪ እንቅሰቃሴ አስቸጋሪ መሆኑን በመግለጽ "በተለይም ነፍሰጡር እናቶችና ህጻናትን አሳፍሮ በመንገዱ ላይ ማሽከርከር አዳጋች ነው" ብሏል።
የመንገዱ አብዛኛው ክፍል የተቆፋፈረ በመሆኑ በየጊዜው በተሽከርካሪ አካል ላይ ብልሽት እንደሚደርሰና ለአደጋም አጋላጭ መሆኑን ተናግሯል ።
"አሁን ያለው የከተማው መንገድ ደረጃ አሶሳን አይመጥንም" ያሉት ደግሞ ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ ትዕዛዙ ታዬ ናቸው፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለከተማው ተጨማሪ የኢንቨስትመንት አማራጭ ይዞ እንደሚመጣ ያመላከቱት አስተያየት ሰጪው አጋጣሚን መጠቀም የሚያስችል የመሠረተ ልማት ግንባታ ማካሄድ እንደሚገባ ጠቁመዋል ።
የአሶሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ኡመር መሐመድ ለከተማው አስፓልት መንገድ ብልሽት ዋነኛ ችግር ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን በሚገባ አለመወጣታቸው መሆኑን ተናግረዋል ።
አስተዳደሩ ህብረተሰቡን ያሳተፈ ስራ አለማከናወኑ፣ በህብረተሰቡ ዘንድ የባለቤትነት ስሜት ማነስ እንዲሁም የውሃ፣ ስልክና መብራት አገልግሎት ተቋማት ተቀናጅተው አለመስራትን በዋቢነት ጠቅሰዋል ።
በተያዘው በጀት አመት በ415 ሚሊዮን ብር የከተማውን አስፓልት ለመጠገንና ደረጃ ለማሻሻል የግንባታ ጨረታ መጠናቀቁን ከንቲባው አስታውቀዋል፡፡
"የመንገዱ ስራም በበጀት አመቱ መጨረሻ ይጠናቀቃል" ብለዋል፡፡
የግንባታ ጥራት ማነስ የአስተዳደሩ ዋነኛ ችግር እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ኡመር ቅንጅታዊ አሰራርን በማስፈን መፍትሔ ለማምጣት ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር ውይይት ተደርጎ መግባባት ላይ መደረሱን ጠቅሰዋል፡፡
ህብረተሰቡ የመንገዱን ግንባታ በባለቤትነት በመከታተል ችግሮች ሲታዩ ተከታትሎ እርምጃ እንዲወሰድ በማድረግ የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡
የአሶሳ ከተማ ከ30 ኪሎ ሜትር በላይ የውስጥ ለውስጥ አስፓልት መንገድ እንዳለው የአስተዳደሩ መረጃ ያመላክታል፡፡