ከሊባኖስ 165 ኢትዮጵያዊያን ወደ አገራቸው ተመልሰዋል - ኢዜአ አማርኛ
ከሊባኖስ 165 ኢትዮጵያዊያን ወደ አገራቸው ተመልሰዋል
አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 25/2012(ኢዜአ) ከሊባኖስ 165 ኢትዮጵያዊያን ዛሬ ወደ አገራቸው ተመልሰዋል።
የውጭ ጉዳይና የሰላም ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎች ለኢትዮጵያዊያኑ አቀባበል አድርገውላቸዋል።
ኢዜአ ከሊባኖስ የመጡት ዜጎች አነጋግሯል።
ወደ አገራቸው የተመለሱት ዜጎች ለተደረገላቸው ድጋፍ አመስግነው መንግስት በአሁኑ ወቅት በሊባኖስ በችግር ላይ ለሚገኙት ዜጎች እንዲደርስላቸው ጠይቀዋል።
በሊባኖስ በነበራቸው ቆይታም የተለያዩ ችግሮች እንደረሰባቸው የተናገሩት ተመላሾቹ፣ መንግስት ለዜጎች መብት መጠበቅ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አመልክተዋል።
ዜጎች የስደት መንገድ እንዳይመርጡና በአገራቸው ሰርተው መለወጥ እንዲችሉ መንግስት ከማቋቋም ባለፈ የሥራ ዕድል በበቂ ሁኔታ መፍጠር እንዳለበት ተናግረዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ፅዮን ተክሉ ዛሬ ከሊባኖስ የተመለሱት ዜጎች በተለያየ ምክንያት ችግር ውስጥ የነበሩና በመንግስትና በሌሎች አካላት ድጋፍ ሲደረግላቸው የቆዩ መሆናቸውን ለኢዜአ ገልጸዋል።
የተመለሱት ዜጎች ወጪያቸውን በራሳቸው መሸፈን የማይችሉ በመሆናቸው ወጪያቸው በሊባኖስ በሚገኙ የበጎ አድራጎት ተቋማት፣ የእምነት ተቋማት፣ ግለሰቦችና ቡድኖች መሸፈኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በጉዞ ትኬት ላይ ቅናሽ ማድረጉንም ጠቁመዋል።
በቤይሩት የሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽህፈት ቤት የተመላሾቹን የጉዞ ሰነድ (ሊሴ ፓሴ) እና የመውጫ ቪዛ የማግኘት ሂደት የማመቻቸት ሥራ ማከናወኑንም አመልክተዋል።
በሊባኖስ ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ምክንያት ኢትዮጵያዊያን ለችግር በመጋለጣቸው በመጀመሪያ ያሉበትን ሁኔታ አውቆ የማረጋጋት ሥራ መሰራቱን ወይዘሮ ጽዮን ጠቅሰዋል።
በሂደት ወደአገራቸው መመለስ የሚፈልጉ ዜጎችን የመለየት ሥራ መከናወኑንና ከመምጣታቸውም በፊት መንግስት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን አስፈላጊውን ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ነው ወይዘሮ ፅዮን ያስረዱት።
በሊባኖስ ባለው ችግር በተለይም ከቤይሩት ወደብ ፍንዳታ በኋላ በተባበሰው የኢኮኖሚ ቀውስ ምክንያት አሰሪዎች የሚያሰሯቸውን ዜጎች ቤይሩት በሚገኘው ቆንስላ ጽህፈት ቤት ጥለዋቸው እንደሚሄዱ ገልጸዋል።
"የኢትዮጵያ መንግስትም ዜጎች መብታቸውና ጥቅማቸው እንዲከበር ለማድረግ ከሊባኖስ መንግስት ጋር በመነጋገር ችግሩ እንዲፈታ የሚያስችል ሥራ እየተከናወነ ነው" ብለዋል።
መንግስት በሊባኖስ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ጥቅማቸው እንዲጠበቅ እየሰራ መሆኑንና ለረጅም ጊዜ በአሰሪዎች ክፍያ ያልተፈጸመላቸው ዜጎች ክፍያቸውን እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህም ሆኖ አሁንም ክፍያቸው ያልተፈጸመላቸው ዜጎች መኖራቸውንና ክፍያቸውን እንዲያገኙ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
ከአሰሪዎች ጋር የሚፈጸም የ"ካፋላ" ስምምነት ዜጎችን ለችግር እንደሚያጋልጣቸው ገልጸው፣ ስምምነቱ ሠራተኞች ቢጎድና ቢንገላቱ ያለ አሰሪዎቻቸው ፍቃድ እንደማይወጡ ጠቁመዋል።
ዜጎች ህጋዊ በሆነ መንገድ ወደውጭ አገር ቢሄዱ መልካም እንደሚሆን ነው ወይዘሮ ጽዮን ያስረዱት።
መንግስት ከሊባኖስ የሚመጡ ኢትዮጵያዊያንን የመመለስ ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልና ዛሬ ማምሻውን ጨምሮ በዚህ ሳምንት 243 ዜጎች ወደ አገራቸው እንደሚመለሱ አመልክተዋል።
"እነዚህ የሚመለሱ ዜጎች የትራንስፖርት ወጪያቸውን በራሳቸው የሚሸፍኑ ናቸው" ብለዋል።
የዛሬን ሳይጨምር ከሰኔ ወር 2012 ዓ.ም ጀምሮ 650 ኢትዮጵያዊያን ከሊባኖስ መምጣታቸውንም ወይዘሮ ጽዮን አስታውሰዋል።
ከተለያዩ አገራት የሚመጡ ኢትዮጵያዊያን የሚቋቋሙበትና የሥራ ዕድል የሚያገኙበት ፕሮጀክት ከሠራተኛ ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዲሁም ከሌሎች አካላት ጋር በመሆን ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ዜጎችን ወደ አገራቸው መመለስ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ባሉበት አገር መብታቸው እንዲጠበቅና በልማት ሥራዎች ላይ ተሳትፎ እንዲያደርጉ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።
ዛሬ ለተመለሱት ዜጎች ድጋፍ ላደረጉ አካላት ወይዘሮ ጽዮን ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት ከተለያዩ አገራት ከ250 ሺህ በላይ ዜጎች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ መደረጉን አክለዋል።