ቀጥታ፡

የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ በደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ጉዳዮች ሚኒስትር ከተመራ የልዑካን ቡድን ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ነሐሴ 25/2012 (ኢዜአ) የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ጉዳዮች ሚኒስትር ኒያል ዲንግ ኒያል ከተመራ የልዑካን ቡድን ጋር ተወያዩ።

የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የልዑካን ቡድኑን ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

በዚህም ሁለቱ አገራት በመንገድና በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት በጋራ መልማት በሚችሉበት ሁኔታዎች ላይ እና በቀጣይ ግንኙነታቸውን የበለጠ ማጠናከር በሚችሉባቸው ሂደቶች ላይ ተወያይተዋል።

በውይይታቸው ከዚህ ቀደም ሁለቱን አገራት በመንገድ እና በድልድይ ለማስተሳሰር የተፈራረሙት ስምምነቶች ተግባራዊ መሆን በሚችልበት መንገድ ላይም ትኩረት አድርገዋል።

በተጨማሪም ከኢትዮጵያ ወደ ደቡብ ሱዳን የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፍ በሚቻልበት ሁኔታ እንዲሁም  ጋምቤላ-አኮቦ-ቦሮ የመንገድ ፕሮጀክትን በጋራ ለመስራት በሚደረጉ ጥረቶች ላይ ተነጋግረዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የደቡብ ሱዳን ሉዑካንን ተቀብለው በማነጋገራቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልፀው፣ የሁለቱን አገራት ወዳጅነት የበለጠ ለማጠናከር እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ጉዳዮች ሚኒስትር ኒያል ዲንግ ኒያል በበኩላቸው "ሁለቱን አገራት በተለያዩ የመሰረተ ልማት ዘርፎች ማስተሳሰር የቀጠናውን ኢኮኖሚ የበለጠ እንዲጠናከር ያደርጋል" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም