በኢትዮጵያ 8 ባህላዊ መድሃኒቶች የኮቪድ-19 ለመከላከልና ለማከም ፈዋሸነታቸው እየተገመገመ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ 8 ባህላዊ መድሃኒቶች የኮቪድ-19 ለመከላከልና ለማከም ፈዋሸነታቸው እየተገመገመ ነው
አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 25/2012 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ኮቪድ-19ን ለማከምና ለመከላከል የሚረዱ ስምንት ባህላዊ መድሃኒቶች ፈዋሽነታቸውን በሳይንሳዊ ዘዴ ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ የምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን አስታወቀ።
የአፍሪካ የባህል መድሃኒቶች ቀን በየዓመቱ ነሃሴ 25 ቀን ታስቦ የሚውል በመሆኑ 18ኛው አህጉር አቀፍ የባህል ህክምና ቀን እየተከበረ ነው።
በዓሉን በማስመልከት የጤና ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ የምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣንና የባህላዊ የህክምና አዋቂዎች ማህበር በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ የምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን የምርት ደህንነት ዳይሬክተር ወይዘሮ አስናቀች አለሙ እንዳሉት ኮቪድን ለመከላከልና ለማከም ''የባህላዊ መድሃኒቶች ጊዚያዊ ጋይዳንስ'' ተዘጋጅቶ የሙከራ ጥያቄዎችን በማስተናገድ ላይ ናቸው።
በሂደቱ ስምንት የሚሆኑ ኮቪድን ለማከምና ለመከላከል የሚያግዙ የባህላዊ መድሃኒቶች ቀርበው በሰው ላይ ሙከራ እንዲደረጉ የሚያስችል የሰነድ ምርመራ እየተደረገባቸው ነው ብለዋል።
የባህል ህክምና አዋቂዎች እነዚህ መድሃኒቶች በተለያዩ የሙከራ ዘዴዎች በማለፍ ውጤት አገኝተንበታል ብለው እውቅና እንዲሰጣቸው ጥያቄ አቅርበዋል።
በመሆኑም ባለስልጣኑ ይህንን ለማረጋገጥ የሰነድ ግምገማ እያካሄደ መሆኑን ጠቁመዋል።
የቀረቡት መድሃኒቶች ሁሉ ወደ ስራ ይገባሉ ማለት ሳይሆን በሳይንሳዊ ዘዴ ፈዋሽነታቸው ተረጋግጦና በሰው ላይ ምንም አይነት ጉዳት እንደማያደረሱ ሲረጋገጥ ብቻ እንደሆነ ጠቁመዋል።
በአገሪቱ በርካታ ለባህል ህክምና የሚሆኑ እፅዋቶችና እውቀቶች ቢኖሩም ትኩረት ስላልተሰጣቸውና በዘመናዊ የምርምር ዘዴ ስላልተደገፉ እስካሁን ወደ ስራ አልገቡም።
ኮቪድ ከተከሰተ በኋላ ለባህላዊ ህክምና ዓለም አቀፍ ትኩረት በማግኘቱና የሰዎችም ፍላጎት በመጨመሩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በተለይ የዩንቨርስቲዎችና ተመራማሪዎች በባህላዊ መድሃኒቶች ላይ በስፋት ጥናትና ምርምር እያደረጉ መሆኑንም ገልጸዋል።
በምርምሩም ተስፋ ሰጪ ምልክቶች እንዳሉ ነው ወይዘሮ አስናቀች የተናገሩት።
በባህላዊ ህክምና እስካሁን አንድም መድሃኒት እውቅና እንዳልተሰጠው የገለጹት ዳይሬክተሯ በአሁኑ ወቅት ግን በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
የጤና ሚኒስቴር የህክምና አገልግሎት ዳይሬክተር ጀኔራል ያዕቆብ ሰማን እንደሚሉት በአፍሪካ 50 በመቶ የሚሆነው ህዝብ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የባህላዊ መድሃኒት ተጠቃሚ ነው።
በኢትዮጵያም አብዛኛው ህዝብ የባህል መድሃኒቶችና ህክምና ተጠቃሚ በመሆኑ ባህላዊ ህክምናን በዘመናዊ ዘዴ እንዲታገዝና ጥቅም ላይ እንዲውል እየተሰራ ነው ብለዋል።
መንግስትም ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት እንደሰጠው የጠቀሱት ዳይሬክተር ጀነራሉ የባህላዊ ህክምና በ10 ዓመቱ የጤና መሪ ዕቅድ ላይ መካተቱን ገልጸዋል።
የእለቱ መከበርም ለባህላዊ መድሃኒትና ህክምና ትኩረት እንዲሰጥና በዘርፉ ያሉ ተማራማሪዎች እንዲበረታቱ እድል ይሰጣል ብለዋል።
የባህል ህክምና አዋቂዎች ማህበር መስራችና ምክትል ጸሃፊ አቶ ሀሚድ አብዳላ እንደሉት ማህበሩ ከኮቪድ ጋር ተያይዞ ከ58 የእጽዋት አይነቶች መድሃኒት በመዘጋጀት እውቅና ለማግኘት አቅርቧል።
በአሁኑ ወቅት ለባህላዊ ህክምና መንግስት ተኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው ማህበሩ በኢንስቲትዩሽን ደረጃ እንዲዋቀር ለቀረበው ጥያቄ አፈጣኝ መልስ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።
በኢትዮጵያ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው ሰው የባህላዊ መድሃኒቶች እንደሚጠቀም መረጃዎች ያሳያሉ።