ቀጥታ፡

የአየር መንገድ አውሮፕላን አብራሪዎች ማህበር ለችግር ለተጋለጡ ወገኖች የምግብ ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 25/2012 (ኢዜአ) የአየር መንገድ አውሮፕላን አብራሪዎች ማህበር ለችግር ለተጋለጡ የህብረተሰብ ክፍሎች የምግብ ድጋፍ አደረገ።

ግምቱ 250 ሺህ ብር እንደሆነ የተገለፀው የማህበሩ ድጋፍ ዱቄት፣ ፓስታ፣ የምግብ ዘይትና ሩዝን ያካተተ ነው።

በዚህም በቦሌ ቡልቡላ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በማህበሩ የትምህርት ቤት ፈንድ ሲደገፉ ለነበሩ 100 ተማሪዎች በዛሬው ዕለት የምግብ ድጋፍ ተደርጓል።

የአየር መንገድ አውሮፕላን አብራሪዎች ማህበር ፕሬዚዳንት ካፒቴን በረከት አባተ የትምህርት ቤት ፈንዱ ከሰኔ 2011 ዓ.ም ጀምሮ መጀመሩን ገልጸዋል።

ከማህበሩ ከአባላት ጋር በመወያየት ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ሲሉ ለትምህርት ቤቱ ተማሪዎች ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን አመልክተዋል።   

ለትምህርት ቤት ፈንዱ የሚውለው ገንዘብ በዋናነት ከአባላት መዋጮ የሚገኝ መሆኑን የጠቆሙት ካፒቴን በረከት፣ ትምህርት ቤቱ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር መምረጣቸውን ተናግረዋል።

በዚህም ማህበሩ የቦሌ ቡልቡላ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ቤተመጻህፍትና ቤተሙከራን የማጠናከርና  ከመስከረም 2012 ዓ.ም ጀምሮ የተማሪዎች የምገባ መርሃግብር ማካሄዱን አመልክተዋል።

በተጨማሪም ተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት እንዲያገኙ የማገዝ ሥራ መስራቱን ነው የገለጹት።

"በኮሮናቫይረስ ምክንያት ትምህርት ቤት በመዘጋቱ ተማሪዎችና ወላጆች መቸገራቸውን በመግለጻቸው በዛሬው ዕለት ይህን ጊዜያዊ ድጋፍ አድርገናል" ሲሉም ካፒቴን በረከት አመልክተዋል።

ከዚህ ቀደም የማህበሩ አባላት በአየር መንገድ በኩል ከደመወዛቸው በቀጥታ ለማህበሩ ያዋጡ እንደነበር ገልፀው፣ በአሁኑ ወቅት ይህ አሰራር መቋረጡ እንቅፋት እንደሆነባቸው ተናግረዋል።

ልጆቹን ለመደገፍና የተቸገሩትን ለመመገብ መዋጮው አስፈላጊ በመሆኑ አየር መንገዱና የሚመለከታቸው አካላት ይህንን ጉዳይ መፍትሄ እንዲሰጡት ጠይቀዋል።    

ማህበሩ በፈንዱ ውጤታማ የሆኑ ተማሪዎችን በአቪዬሽን ዘርፍ ወጪያቸውን ሸፍኖ ለማሰልጠን ማቀዱንም ነው ካፒቴን በረከት አያይዘው ገልጸዋል።

ድጋፍ ካገኙ ተማሪዎች መካከል በቦሌ ቡልቡላ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ10ኛ ክፍል ተማሪ ለይኩን ሲሳይ አንዱ ነው።

በገቢ ማጣት ምከንያት እህቱን ሰርቶ ለማስተማር ሲል የራሱን ትምህርት ለዓመታት አቋርጦ እንደነበር ያስታውሳል።

የአየር መንገድ አውሮፕላን አብራሪዎች ማህበር በትምህርት ፈንዱ በኩል የተማሪዎች ምገባ ሲጀምር እሱም ከእህቱ ጋር ዳግም ትምህርቱን ለመቀጠል ችሏል።

"የተማሪዎች ደንብ ልብስና የመማሪያ መሳሪያዎች በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፤ ምግባችን ደግሞ በማህበሩ በኩል ሲሸፈን እኔና እህቴ ካለሃሳብ በመማራችን ውጤታማ ሆነናል" ብሏል።

የተማሪዎች ምገባ መርሃግብሩ እንደእሱ ትምህርት አቋርጠው የነበሩ ተማሪዎች ዳግም ወደትምህርት ዓለም እንዲመለሱ ማድረጉን የጠቆመው ተማሪ ለይኩን፣ በዛሬው እለት በማህበሩ በኩል የተደረገላቸው ድጋፍ ተጠናክሮ ለሌሎች እንዲደርስ ጠይቋል።

ማህበሩ ለ100 የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች ቁርስና ምሳ ሲመግብ መቆየቱን የገለጹት ደግሞ የቦሌ ቡልቡላ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የአደረጃጀትና ትምህርት ፕሮግራም ምክትል ርዕሰ መምህር ወይዘሮ ቤተልሔም ወንድሙ ናቸው።  

"በኮሮናቫይረስ ምክንያት ትምህርት ቤት ተዘግቶ ምገባው ሲቋረጥ በርካታ ተማሪዎች ወደእኔ መጥተው ይጠይቁኝ ነበር" ያሉት ወይዘሮ ቤተልሄም፣ በእዚህም ለማህበሩ ጥያቄ ማቅረባቸውን አመልክተዋል።

በዚህም ማህበሩ በዛሬው ዕለት ለተማሪዎቹ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸው፣ እስከዛሬ ለትምህርት ቤቱና ለተማሪዎች ሲያደርገው የነበረውን ድጋፍ በቀጣይም አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም