ቀጥታ፡

የአውሮፓ ኀብረት ለኢጋድ አባል አገራት የኮሮናቫይረስ መከላከያ ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ ፣ነሐሴ 25/2012 (ኢዜአ) የአውሮፓ ኀብረት ለኢጋድ አባል አገራት የ60 ሚሊዮን ዩሮ ግምት ያለው የኮቪድ- 19 መከላከያ ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።

በድጋፉ ወቅት የኢፌዲሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው፣ የኢጋድ ዋና ፀሃፊ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ፣ የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰን ጨምሮ ሌሎች ዓለም አቀፍና የአፍሪካ ተወካዮች ተገኝተዋል።  

ለኮቪድ-19 መከላከያ የተደረገው የቁሳቁስ ድጋፍ 60 ሚሊዮን ዩሮ ወጭ የተደረገበት ሲሆን ኢትዮጵን ጨምሮ ለስምንት የኢጋድ አባል አገራት መሆኑ ተገልጿል።

በድጋፉም ሰርጂካል ማስክ፣ የእጅ ጓንቶች፣ የጭንቅላትና የፊት መሸፈኛዎች ተካተውበታል።  

የቴስት ኪቶች፣ ጫማ መሸፈኛ አልባሳትና አምቡላንሶች ተጋላጭ ወደ ሆኑ የቀጠናው አካባቢዎች እንደሚላኩ ነው የተገለጸው።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው፤ የአውሮፓ ህብረት ለቀጠናው አገራት የኮሮናቫይረስ መከላከያ እያደረገ ላለው ድጋፍ በኢፌዲሪ መንግስት ስም ምስጋና አቅርበዋል።

በዛሬው እለት የተደረገው ድጋፍም ኀብረቱ በቀጣናው እያደረገ ያለውን ቀጣይነት ያለው እገዛ የሚያመላክት ነው ብለዋል።

ድጋፉ ለኮሮናቫይረስ ተጋላጭ ለሆኑ አባል አጋራት እገዛው ላቅ ያለ መሆኑንም አቶ ገዱ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት በሚችለው አቅም ሁሉ ድጋፉ ወደ ሌሎች አጋሮች እንዲሰራጭ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ይወጣል ሲሉም አረጋግጠዋል።

የኢጋድ ዋና ፀሃፊ ወይቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) በበኩላቸው በአባል አገራቱ ውስጥ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ በመሆኑ ኢጋድ ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል።

በቀጣይም ኢጋድ ከሌሎች አካላት ጋር በመተባበር በአህጉሪቱ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት እንደሚጥር አረጋግጠዋል።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግስት እየተስፋፋ የመጣውን የኮቪድ-19 ቫይረስ ለመከላከል ከአጋር አካላት ጋር በትብብር በመስራት ላይ መሆኑን አስረድተዋል።

የአውሮፓ ኀብረትም ቀጣናውን ለመደፍ ያደረገውን እንቅሰቃሴ አድንቀው ቫይረሱን ለመቋቋም በጋራ ከመስራት ውጭ ሌላ አማራጭ የለም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም