ቀጥታ፡

በጋምቤላ፣ አፋርና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ የብልጽግና ፓርቲ አመራሮች የተሳተፉበት ስልጠና ተጀመረ

ጋምቤላ/ሰመራ/አሶሳ፣ ነሐሴ 25/2012(ኢዜአ) በጋምቤላ፣ አፋርና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች የተሳተፉበት የአቅም ግንባታ ስልጠና ተጀመረ።

ስልጠናው በጋምቤላ ከተማ ሲጀመር የክልሉ የፓርቲው ሥራ አስፈፃሚ  አቶ ኡሞድ ኡጁሉ  "እንደ ሀገር የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ቀጣይነት በማረጋገጥ የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የፓርቲው አመራሮች ተግተው ሊሰሩ ይገባል "ብለዋል።

ባለፉት ዓመታት ክልሉ ያመጣቸውን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ለውጦች ለማስፋትና ክፍተቶችን ለማስተካከል ከአመራሩ ያለሰለሰ ጥረት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

በተለይም ሀገራዊ አንድነትን በማጠናከር የህዝቡን ብሎም የመጪውን ትውልድ ጥቅምና ፍላጎት በዘላቂነት ለማስጠበቅ በ''መደመር'' እሳቤ የተቀየሰውን የለውጥ ጉዞ ወደ ፊት ለማራመድ አመራሩ በቁርጠኝነት ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የብልጽግና ፓርቲው ቀደም ሲል የነበረውን የአግላይና ከፋፋይ የፖለቲካ ስርዓት በማስቀረት መላውን የኢትዮጵያ ህዝቦችን በእኩልነት በማቀፍና በማሳተፍ የሀገሪቱን የብልጽና ጉዞን በማራመድ ላይ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

ፓርቲው ተከታታይ አቅም ግንባታ ስራዎችን በማካሄድ የተቀየሰውን የለውጥና የብልጽግና ጉዞ የሚያፈጽም አመራር የማፍራት ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቅሰው የዕለቱ ስልጠናም የዚሁ አካል መሆኑን አስታውቀዋል።

የጋምቤላ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ባንቻየሁ ድንገታ በበኩላቸው የፓርቲው አመራሮች የአደናቃፊ ኃይሎች ዓላማ በመቀልበስ የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ለማራመድ ጠንክረው እንዲሰሩ አሳስበዋል።

አመራሮቹ በአምስት ቀናት የስለጠና ቆይታቸው በብልጽግና እሳቤ ፣በኢትጵያ ህዝብ ትግል ውስጥ የብልጽግና ታሪካዊ አሻራ፣ በስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫና ፖለቲካ ሁኔታ ዙሪያ ውይይት እንደሚደረጉ ይጠበቃል።

በስልጠናው ከክልል፣ ዞንና ወረዳ  የተወጣጡ ከ350 በላይ የብልፅግና ፓርቲ አመራሮች እየተሳተፉ ነው።

በተመሳሳይ በአፋር ክልል የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች የተሳተፉበት ስልጠና  በሰመራ ከተማ ተጀምሯል።

ከዛሬ ጀምሮ ለአምስት ቀናት በሚቆየው ስልጠና ለቀጣይ ተልዕኮዎች ስኬታማነት ወጥ በሆነ መንገድ ከማዘጋጀት ባለፈ ሀገሪቱን ወደፊት ለማሻገር የሚያስችል የፓርቲ ቁመና ለማጠናከር የተመቻቸ መሆኑ ተገልጿል።

አመራሮቹም አቅማቸውን በመገንባት የሚያጋጥሙ ፈተናዎች ተቋቁመው ሀገራዊ ለውጥና የብልጽግና ጉዞ በመምራት ከዳር እንዲያደርሱ ለማትጋት ጭምር እንደሆነም ተመልክቷል።

ከአመራሮቹ ቀጣይ ክልላዊ ተልዕኮና ቁልፍ ተግባራት ዙሪያ በፓርቲው ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ማብራሪያ እንደሚሰጥም ታውቋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ  የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ስልጠና  ሲጀመር የፓርቲው ከፍተኛ አመራር አቶ አሻድሊ ሃሰን  የስልጠና ዓላማ አመራሩ ራሱን በማብቃት ፈተናዎችን ተቋቁሞ ተልዕኮውን በሚገባ እንዲወጣ ማገዝ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡


ክልሉ ብሎም ሀገሪቱ ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ በሚገባ እንዲገነዘቡ ይደረጋል ብለዋል፡፡


የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኢስሃቅ አብዱልቃድር በበኩላቸው ስልጠናው አመራሩን በዕውቀትና ክህሎት በማጠናከር የብልጽግና ጉዞ እንዲሳካ ስንቅ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡

በስልጠናው 200 ለሚሆኑ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች እየተሳተፉ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም