ከሊባኖስ 165 ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው ተመለሱ - ኢዜአ አማርኛ
ከሊባኖስ 165 ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው ተመለሱ
አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 25/2012(ኢዜአ) በሊባኖስ በአስቸጋሪ ህይወት ውስጥ የነበሩ 165 ኢትዮጵያውያን ዛሬ ወደ አገራቸው ተመለሱ፡፡
ኢትዮጵያውያኑ ወደ አገራቸው የተመለሱት በግለሰቦች፣ ግብረ ሰናይ ድርጅቶችና ቡድኖች በተደረገላቸው የትራንስፖርት ወጪ ነው፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለተመላሾቹ የአውሮፕላን ቲኬት ቅናሽ በማድረግ መተባበሩ ተገልጿል፡፡
በቀጣይም በራሳቸው ሙሉ ወጪ 243 ኢትዮጵውያን ወደ አገራቸው ይመለሳሉ ተብሏል፡፡
ወደ አገራቸው ለመመለስ ከ650 በላይ ዜጎች መመዝገባቸውም ተመልክቷል፡፡
መንግሥትም በሊባኖስ የሚስተዋሉትን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮችን ተከትሎ ዜጎች ወደ አገራቸው ለመመለስ ጥረት እያደረገ መሆኑ ተነግሯል፡፡
ተመላሾቹ ቦሌ አለም አቀፍ አየር መንገድ ሲደርሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የስራ ኃላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡
መንግሥት ከጥቅምት 2012 ጀምሮ 2ሺህ 300 ዜጎችን ከሊባኖስ ወደ አገራቸው መልሷል፡፡
ሊባኖስ በገጠማት የኢኮኖሚ ቀውስ፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝና በቅርቡ ቤይሩት ወደብ ላይ የደረሰው ፍንዳታ ተዳምሮ ችግር ውስጥ ወድቃለች፡፡