ቀጥታ፡

የፌዴራል መንግስት የመሬት ይዞታ አያያዝን ለማዘመን የሚያስችል ስራ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ 25/2012 (ኢዜአ) የፌዴራል መንግስት የመሬት ይዞታ አያያዝን ለማዘመን የሚያስችል ስራ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ።

ለ311 ተቋማት መረጃ ተደራጅቶ ካርታ መዘጋጀቱም ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ የመሬት ባንክና ልማት ኮርፖሬሽንና የኢትዮጵያ ጂኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር የፌዴራል መንግስት የመሬት ይዞታን የሚያዘምን ስራ በማከናወን ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ሶስት የስትራተጂ አቅጣጫዎችን በመያዝ የተቋቋመው የኢትዮጵያ የመሬት ባንክና ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር ወይዘሪት ሌንሳ መኮንን እንደገለጹት፤ መሬት ለሚፈለገው ልማት እንዲውል ዘመናዊ የመረጃ አያያዝ ስርዓት እየተፈጠረ ነው።

ኮርፖሬሽኑ የፌዴራል መንግስት ተቋማትን የመሬት ይዞታ መረጃ በአንድ ቋት በማሰባሰብ ለውሳኔ አሰጣጥ በሚያስችል መልኩ እያዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል።

መረጃውን በማደራጀት የአዋጭነት ጥናት በማድረግና በመተንተን መሬትን ማልማትና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታውን ለማሳደግ ጥረት በመደረግ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

የተቋማቱን የመሬት መረጃ ማደራጀት፣ የአዋጭነት ጥናት ማጥናትና ልማት ላይ መዋሉን ማረጋገጥ የኮርፖሬሽኑ ስትራተጂክ አቅጣጫ መሆኑንም አብራርተዋል።

የኮርፖሬሽኑን ዓላማ ለማሳካት የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ናቸው  ያሉት ወይዘሪት ሌንሳ፤ ከኢትዮጵያ ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር የመሬት ይዞታ መረጃ እየተሰበሰበ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ጂኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቱሉ በሻ በበኩላቸው የፌዴራል መንግስት የመሬት አጠቃቀም ሽፋን ካርታ እየተዘጋጀ መሆኑን አመልክተዋል።

የተቋማቱ የካርታ ዝግጅት ስራ ከአዲስ አበባ መጀመሩን አመልክተው፤ በመላ አገሪቱ እስከ መጪው ዓመት አጋማሽ ድረስ እንደሚጠናቀቅ ገልጸዋል።

ስራው ከተጀመረበት ከሰኔ 2012 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን ድረስ የ311 ተቋማት የመሬት ይዞታ ካርታ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

ከኢትዮጵያ የመሬት ባንክና ልማት ኮርፖሬሽንና ከኢትዮጵያ ጂኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የተውጣጡ አባላትን የያዙ ሰባት ኮሚቴዎች ተቋቁመው ስራውን እያከናወኑ መሆናቸውንም ዶክተር ቱሉ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ የመሬት ባንክና ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር ወይዘሪት ሌንሳም የተቋቋመው ኮሚቴ የመሬት መረጃ አያያዝ ሂደቱን በማቀላጠፍ ረገድ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው ብለዋል።

በሁለቱ ተቋማት አማካኝነት እየተካሄደ ያለው በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚገኙ የፌዴራል መንግስት ተቋማት የመሬት ይዞታ የካርታ ዝግጅት 60 በመቶ መድረሱን መረጃዎች ያመለክታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም