ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ሰራተኞች "ለገበታ ለሀገር '' ፕሮጀክት የአንድ ወር ደሞዛቸውን ለገሱ

አዲስ አበባ ነሀሴ 24/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ሰራተኞች "ለገበታ ለሀገር ''ፕሮጀክት" የአንድ ወር ደሞዛቸውን ድጋፍ አደረጉ። የባለስልጣኑ ሰራተኞችና አመራሮች የሸገርና የእንጦጦ ፕሮጀክቶችን ዛሬ ጎብኝተዋል።

ሸገርን በማስዋብ ፕሮጀክት የተገኘውን ልምድ በአገር ደረጃ ማሳደግ ዓላማ ላደረገው “ገበታ ለሀገር” ለተሰኘው ፕሮጀክት የባለስልጣኑ ሰራተኞችና አመራሮች ደሞዛቸውን ለግሰዋል።

ሰራተኞቹ ግንባታቸው ለሚካሄደው የጎርጎራ፣ ወንጪና ኮይሻ ፕሮጀክቶች ደሞዛቸውን የለገሱት አዲስ አበባን እንደ ስሟ አዲስ እናደርጋታለን የሚለው ሃሳብ  በሸገር ፕሮጀክት ውጤት ማምጣቱን በመመልከታችን ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ የእንጦጦና የሸገር ፕሮጀክቶች በተጠናቀቁበት ዓመት ተጀምረው በመጠናቀቅ  ውጤት እንደተመዘገበባቸው አስታውቀዋል።

ፕሮጀክቶቹ በየትኛውም የዓለም ክፍል ካሉ ፓርኮች በጥራትም ሆነ በጊዜ ተወዳዳሪ መሆናቸውን ገልጸዋል።  

ፕሮጀክቶቹ በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ እንዳይጠናቀቁ የሚያደርጉ በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም፤ጠንካራ አመራር በመስጠት መጠናቀቅ እንደሚቻል ያሳዩ ናቸው ብለዋል።

ፕሮጀክቶችን ለማስፈጸም በርካታ አካላት እገዛ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

ከሰራተኞቹ አንዳንዶቹ በሰጡት አስተያየት ፕሮጀክቶቹ በዚህ ፍጥነት ተሰርተው ለፍፃሜ መብቃታቸው የሚያስደንቅ መሆኑን ገልፀው፣ ልምዱ ለመንገድ ልማት ዘርፍ ትምህርት የሚወሰድበት ነው ብለዋል።

በትናንሽ ጉዳዮች ላይ መጠመድን በመተው በትላልቅ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ መሰል ፕሮጀክቶች እንዲሳኩ ሁሉም ድጋፍ ሊደረግ እንደሚገባም ተናግረዋል።

የተጀመረን ነገር በአጭር ግዜ ማለቁ ስራው ለመንግስትም ሆነ ለመንግስት ሰራተኛው አስተማሪና ተነሳሽነትን የፈጠረ ነው ያለው እንደሻው ተስፋዬ ነው፡፡

 አቶ ዋለልኝ መኩሪያ በበኩሉ ይህ ፕሮጀክት በሀገራችን ባለሞያዎች መሰራቱ  በየግዜው

አንዱ የጀመረውን ስራ ከግብ ለማድረስ  መሰረት የሚጥል ነው ብለዋል፡፡

ለመንገዶች ባለስልጣን የሚሰራቸውን ፕሮጀክት በጥራትና በግዜው  መጨረስን ያስተማረ መሆኑን የተናገረው ደግሞ አብርሃም አማረ ነው፡፡

                                      

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም