ቀጥታ፡

ለውጡን የሚያስቀጥሉ አመራሮችን ማብቃት ቀዳሚ ትኩረት ተሰጥቶታል - የደቡብ ብልጽግና ፓርቲ

ሐዋሳ ነሐሴ 24/2012 (ኢዜአ) በሃገሪቱ የተጀመረውን የለውጥ ሂደት ቀጣይነትና ውጤታማነት በማረጋገጥ ሃገራዊ ግቡንና የህዝብን ተጠቃሚነት ለማሳካት ብቃት ያለው አመራር ለማፍራት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ የደቡብ ብልጽግና ፓርቲ አስታወቀ።

ፓርቲው 550 የአሰልጣኝ አመራሮች የሚሳተፉበት ስልጠና በሐዋሳ ከነገ ጀምሮ ለተከታታ አምስት ቀናት እንደሚሰጥ የደቡብ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ጥላሁን ከበደ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

በለውጥ ሂደቱ በተወሰዱ የሪፎርም ስራዎች ሃገሪቱ ለማመን የሚከብዱና ለነገ ሥራ ስንቅና አቅም የሚሆኑ ስኬቶች የተመዘገቡ ሲሆን ከእነዚህም በታላቁ ህዳሴ ግድብ፤በአንድነት ፓርክና የሌሎችም ትልልቅ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ታሪካዊ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡

ከለውጡ ባሻገር ህዝብንና ሃገርን አደጋ ላይ የሚጥሉ ፈተናዎች በተለይ በሶስቱ ሰኔዎች የገጠሙ ቀውሶች የሚረሱ ባይሆኑም በለውጡ አመራርና በህዝቡ ብርታት መክሸፉን ተናግረዋል።

ከዚህ በፊት ከከፍተኛ አመራር እስከ አባሉ ድረስ የፓርቲው ዕሳቤና ህገ-ደንብ ዙሪያ ስልጠናዎች መሰጠታቸውንና ተፈጥረው የነበሩ ብዥታዎችን በመቅረፍ ለውጦች መመዝገባቸውንም ገልጸዋል።

“የለውጥ ሂደት መሠረታዊ ዓላማና ግብ የተረዳ እንዲሁም በዲሲፕሊን የታነጸ የታለመውን የብልጽግና ጉዞ በማሳካት የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ብቃት ያለውን አመራር ለማፍራትና የሚያስችል ስልጠና ነው” ብለዋል፡፡

የተፈለገውን ውጤት እንዲመዘገብ ዓለም አቀፋዊ፤ሃገራዊና አካባቢያዊ ሂደቶችን ተረድቶ ብቁ አመራር የሚሰጥ ኃይል በስልጠና ለማብቃት ፓርቲው ቁልፍ ተግባር አድርጎ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከዚህ በፊት በተደረጉ ኮንፈረንሶች ከፓርቲው ዲሲፕሊንና ደንብ አንጻር በአመራሩ መካከል የተፈጠሩ የአስተሳሰብና የተግባር መላላቶችን በመለየት ፖለቲካዊ ርምጃዎች መወሰዳቸውን ገልጸው አሁን የሚሰጠው ስልጠና ወቅታዊ ሁኔታን ተረድቶ እንዲመራ ተጨማሪ አቅም ለመፍጠር የታሰበ መሆኑን ነው የጠቆሙት።

“በተለይ በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች የሚነሱ የመዋቅርና የአደረጃጀት ጥያቄዎች አላስፈላጊ ቀውስና መናቆር ሳያስከትሉ እንዲመለሱ መንግስት ጥረት እያደረገ ነው” ያሉት አቶ ጥላሁን በተለያዩ ቦታዎች በአመራሩ ጠንሳሽነት የሚደረጉ ህገወጥ እንቅስቃሴዎች መታረም እንዳለበት ተናግረዋል።

ሁኔታዎችን ተረድቶ የፓርቲውን ራዕይ የሚያሳካና ቀጣይ ተልዕኮውን የሚወጣ ጠንካራ የአመራር ስርዓት መፍጠር የዚህ ስልጠና ዋና ዓላማ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

የፓርቲው ታሪካዊ አሻራ፤ተልዕኮና ዕሳቤ እንዲሁም ወቅታዊ ፈተናዎች እንድምታዎችና የመሻገሪያ ስልቶች በሚል በሁለት ምዕራፍ በተዘጋጁ ሰነዶች ስልጠናው እንደሚካሄድ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም