ቀጥታ፡

የሞጆ ደረቅ ወደብ ምዕራፍ አራት በቀጣይ ዓመት መልማት ይጀመራል

አዲስ አበባ ነሐሴ 23/2012 (ኢዜአ)የሞጆ ደረቅ ወደብ ምዕራፍ አራት የማልማት ስራ በቀጣይ ዓመት የመጀመሪያዎቹ ወራት እንደሚጀመር ተገለጸ።

በምዕራፉ ዘመናዊ አሰራሮችን በመዘርጋት የወደቡን አገልግሎት ቀልጣፋና ፈጣን ይደረጋል ተብሏል።

በወደቡ ቀደም ሲል በተካሄዱት ምዕራፎች የተርሚናል፣ የተርሚናልና ኤሌክትሪክ ኃይል፣ የመጋዘን ግንባታን ተከናውነዋል።

የሞጆ ወደብና ተርሚናል ዳይሬክተር አቶ ደረጀ ሚደቅሳ ለኢዜአ እንደገለጹት በወደቡ በምዕራፉ  የወጪና ገቢ ንግድን ለማሳለጥና በወደቡ ዘመናዊ አሰራሮችን የሚዘረጉ ተግባራት ይከናወናሉ።

ከነዚህም ዘመናዊ መቆጣጠሪያ፣ የደረቅና ፍሳሽ ማስወገጃ አገልግሎት፣ የኤሌክትሮ መካኒካል ልማት፣ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ የሰው ሃይል ልማትይገኙበታል ብለዋል።

ወደቡ በኢትዮጵያ መንግሥትና በዓለም ባንክ የሚለማ ሲሆን፣ በመንግሥት አቅም የሚለማው በመስከረም ወር ሥራው ይጀመራል።

በተመሳሳይ የዓለም ባንክ ለሚካሄደው ሥራ ዓለም አቀፍ ጨረታ ተካሂዶ በቀጣይ ሶስት ወራት ማልማት ይጀመራል ብለዋል።

አሰራሩን በኤሌክትሮኒክስ የታገዘና ዘመናዊ በማድረግ ተደራሽነትና መረጃ ልውውጥን ፈጣን ያደርጋል ተብሏል።

የማልማት ስራው ሲጠናቀቅ የአገልግሎት መጠንና ዓይነት እንደሚያድግ  ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

የወደቡ ኮንቴነር አቀማመጥ ሙሉ ለሙሉ በዘመናዊ አሰራር ባለመደራጀቱ በቀላሉ ለማግኘት አዳጋች የሚሆንበት ወቅት እንዳለ ገልጸዋል።

ወደ ዘመናዊ የተርሚናል አሰራር ሲገባ ባለሙያው በቀላሉ ኮንቴነሩን ማግኘት ይችላል፤ ይህም ፈጣን የትራንሲት አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል።

ወደቡ ለ600 የአካባቢው ወጣቶች ሥራ  መፍጠሩን አቶ ደረጀ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም